Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የአፍሪካ ህፃናት ቀን በፓናል ውይይትና የህፃናት ፖርላማ ሪፖርትን በማዳመጥ ተጠናቀቀ
የአፍሪካ ህፃናት ቀንን ምክንያት በማድረግ የህፃናትን ሁለንተናዊ መብትና ደህንነት ማረጋገጥ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከተለያዩ ሴክተር ቢሮ ኃላፊዎች ጋር በተደረገው የፓናል ውይይት የሁሉም ክልሎችን የህፃናት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት በመስማት ተጠናቋል።
በትምህርት ሴክተር በኩል በገጠር የቅድመ-አንደኛ ትምህርት ተደራሽነትን ማሳደግ፣ ታዳጊ ሴቶች ትምህርት እንዳያቋርጡ በትምህርት ቤቶች የንጹህ ውሃ፣ የሽንት ቤትና የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ አቅርቦትን ማሻሻል፣ የትምህርት ቤት ምገባን ማስፋፋት እና የተዘጉ ትምህርት ቤቶችን ዳግም መክፈት ላይ የተሰሩ ስራዎች ቀርበዋል። በጤናው ዘርፍ ደግሞ የጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ የተደረጉ የክትባት ዘመቻዎች፣ መቀንጨርና መቀጨጭን ለመከላከል የተወሰዱ የስነ-ምግብ እርምጃዎች፣ በጤና ተቋማት የንጹህ ውሃ አቅርቦት እና ለአካል ጉዳተኞች የሚሰጡ የጤና አገልግሎቶች ተዳስሰዋል። የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ቢሮም ህፃናት ድምጻቸውን የሚያሰሙባቸው የህፃናት ፓርላማዎች መቋቋማቸውን፣ በማሳደጊያ ተቋማት ላይ ያለው ቁጥጥር መጠናከሩን እና በመንግስት በጀት ውስጥ ለህፃናት መብትና ደህንነት በቀጥታ ፈንድ መመደቡን የማረጋገጥ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጿል።

በፍትህ ሴክተር በኩል ደግሞ ለጥቃት ሰለባ ህፃናት ጥበቃ የሚያደርጉ “ምቹ የህፃናት ችሎቶች” መስፋፋታቸው፣ የጥቃት መዝገቦች አፋጣኝ ውሳኔ የሚያገኙበት አሰራር መዘርጋቱ እና በሩቅ አካባቢ ላሉ ህፃናት የሚሰጥ ነፃ የህግ ድጋፍ ተደራሽነት ተብራርቷል።የፓናል ውይይቱ ማጠቃለያ የህፃናትን መብት ለማስከበር በሁሉም ሴክተሮች (ትምህርት፣ ጤና፣ ፍትህና ማህበራዊ) መካከል የተቀናጀ ስራ መስራት እንደሚገባ አሳይቷል። በተጨማሪም ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ የህፃናት ፖርላማ አባላት በአመቱ የታሠሩ ስራዎችን አፈፃፀም ያቀረቡ ሲሆን በሪፖርቱ የተገኙ መልካም ተሞክሮችን በማጠናከር ድክመቶችን ለይቶ በማመላከት ለቀጣይ ተመራጭ የህፃናት ፖርላማ አባላት መደላድልን በመፍጠር ተጠናቋል።
