Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
”የፕሬዝደንሺያል የአመራርነት ስልጠና ሴት መሪዎቻችን በዕውቀት፣ በክህሎትና በራስ መተማመን በልጽገው አገራቸውን ይበልጥ እንዲያገለግሉ ለማስቻል የተወጠነ ትልቅ አገራዊ ራዕይ ነው” – ክብርት ሒክማ ከይረዲን
ክብርት ሚንስትር ዴኤታዋ ይህንን ያሉት የምዕራፍ 2 የፕሬዚደንሻል አመራርነት ስልጠና የማጠቃለያ ፕሮግራምና የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሴቶች አቅም ማጎልበት እና የሥርዓተ-ጾታ እኩልነት ፖሊሲ ትውውቅ መርሃ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።
በእለቱም የሴቶች በአመራርነት ቦታዎች ላይ መገኘት ለአገር ዕድገትና ለፍትሐዊ ሥርዓት ግንባታ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩት ሚንስትር ድኤታዋ መንግስትም የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ረገድ የሚታይና ለውጥ ማምጣት የቻለ ስራ እየሰራ ስለመሆኑ ጠቁመዋል። የኅብረተሰቡ ግማሽ አካል የኾኑትን ሴቶች ሁለንተናዊ አቅም ሳይገነባ ሀገርን ወደሚፈለገው ደረጃ ማሻገር እንደማይቻል የተናገሩት ሚንስትር ድኤታዋ ሀገራዊ ግቦችን ለማሳካት የሴቶችን አቅም ማጎልበት ለነገ የማይባል ተግባር ስለመሆኑ አፅኖት ሰጥተዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የተጀመሩ ጥረቶችን በተጠናከረ መንገድ ለማስኬድ ከፊታችን በሚካሄደው በሀገራዊ ምክክር ላይ ሴቶች ንቁ ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደሚገባ ክብርት ሒክማ አሳስበዋል።
ግጭቶች ከፍ ሲልም ጦርነቶች ሲፈጠሩም ሴቶች ግንባር ቀደም ተጋላጭ እንደመሆናቸው መጠን ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በሚደረጉ ሂደቶች ውስጥ የሴቶችን ተሳትፎ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን የተናገሩት ክብርት ሒክማ ሀገራዊ ምክክር ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ አንዱ መንገድ እንደመሆኑ ከስርዓተ-ጾታ ረገድ ትርጉም ያለው አካታችነትን፣ ፍትሀዊነትንና እኩልነትን ሊያረጋግጥ እንደሚገባ አፅኖት ሰጥተዋል። ሴቶች በምክክር ሂደቶች ውስጥ ሙሉና ትርጉም ያለው ተሳትፎን በማድረግ ወቅታዊና ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮቻችንን በጋራ ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱም ክብርት ሚንስትር ድኤታዋ ጥሪ አቅርበዋል።
በማጠቃለያ መርሃ ግብሩም በፕሬዝዳንሺያል ሁለተኛ ምእራፍ የአመራሮች ስልጠና ላይ ለተሳተፉ አሰልጣኞች፣ልምድና ተሞክሯቸውን ላጋሩ ተፅእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እንዲሁም በማስተባበር ሂደቱ ለተሳተፉ መንግስታዊና መንግስታዊ ላልሆኑ አጋር ድርጅቶች የምስጋና ሰርተፍኬት ተበርክቷል። በፕሬዝደንሺያል የአመራርነት ስልጠናም በ አምስት ዙር 164 ሴት አመራሮችና እጩ ሴት አመራሮች መሳተፋቸው ተጠቁሟል።
