የወር አበባ ጤናና ንፅህና መጠበቂያ ምርት ጥራት፣ ተመጣጣኝነትና ተደራሽነትን ለማሻሻልና ለሴቶች ክብር የሚመጥን ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ባለድርሻ አካላት በቅንጀት እንዲሰሩ ጥሪ ቀረበ።

በወር አበባ ጤናና ንፅህና መጠበቂያ (MHH) ምርቶች ጥራት እና የገበያ ልማት ላይ ያተኮረ ብሔራዊ የምክክር መድረክ በሀዋሳ ከተማ ተካሂዷል።

‎‎በመድረኩ ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ፤ የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ እጦት ሴት ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ፣ ሴት ሰራተኞችም ከስራና ከማህበራዊ ተሳትፎ እንዲገለሉ በማድረግ ከግለሰቧ አልፎ የቤተሰብን፣ የማኅበረሰብንና ሀየገርን አጠቃላይ አቅም ይጎዳል ብለዋል። ለስርዓተ-ጾታ እኩልነትም ትልቅ እንቅፋት እንደሚፈጥር ገልፀዋል። ‎የወር አበባ ጤናና ንፅህና የጤና ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ የሴት ልጅ ክብርና የፆታ እኩልነትና ማህበራዊ አካታችነት እንዲሁም የትምህርት እና የኢኮኖሚ ተሳትፎ መሠረት መሆኑ ገልጸዋል። በቅርቡ በጸደቀው አዲሱ የሴቶች ማብቃትና የፆታ እኩልነት ፖሊሲ ውስጥም ትልቅ ትኩረት መሠጠቱን ጠቁመዋል።

ክፍተቶችን ለመፍታት ሀገራዊ ፕሮግራም ተቀረጾ ሚኒስቴሩና የጤና ሚኒስቴር በጋራ የሚመሩት የመንግስትና የግል ተቋማት ፎረም ተቋቁሞ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል። ከUNFPA ኢትዮጵያ፣ ከኢኤጌት ሆልዲንግስ (ኢስት አፍሪካ ጌት)፣ ከኢትዮጵያ የስነ-ተዋልዶ ጤና ማኅበራት ህብረት (CORHA) እና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር ዘላቂ የወር አበባ ጤና ሥርዓት ለመገንባት ርብርብ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል። መንግስት ችግሩን ለመቅረፍ አበረታች እርምጃዎችን እየወሰደ ቢሆንም፤ የምርቱን አቅርቦት ለማሳደግ፣ ተመጣጣኝና ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆንና ተደራሽ ለማድረግ የተጀመረው የጋራ ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አፅዕኖት ሰጥተዋል።

‎‎የመድረኩ ዋና ዓላማ በወር አበባ ጤና እና ንፅህና ላይ ሀገራዊ መነቃቃትን መፍጠር፣ የተቀናጀ እርምጃን ማጠናከር እንዲሁም በፌደራል እና በክልል ደረጃ በመንግስት ተቋማት፣ ተቆጣጣሪ አካላት፣ በግል ባለሀብቶች እና የሲቪል ማህበራት መካከል ያለውን ቅንጅት ማሳደግ እንደሆነ ገልፀዋል። በመሆኑም ባለድርሻ አካላት የወር አበባ ጤናና ንፅህና መጠበቂያ ምርት ጥራት፣ ተመጣጣኝነትና ተደራሽነትን ለማሻሻልና ለሴቶች ክብር የሚመጥን ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት በቅንጀት እንዲሰሩ ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ ጥሪ አቅርበዋል።
‎

Please follow and like us: