‎‎የህፃናት ኢንቨስትመንት ፈንድ ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ የህፃናት መብትና ጥበቃ ስርዓት ማጠናከሪያ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ከህፃናት ኢንቨስትመንት ፈንድ ፋውንዴሽን ዋና መስራች ሰር ክሪስ ሆን እና ልዑካቸው ጋር በኢትዮጵያ የህፃናት ጥበቃ ስርዓት ዙሪያ መክረዋል።
‎‎በውይይቱም ፋውንዴሽኑ በሀገሪቱ የህፃናት ያለዕድሜ ጋብቻን፣ ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችንና የሴት ልጅ ግርዛትን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ላይ ሰፊ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል። ለህፃናት ጥበቃ ስራዎች ውጤታማነት የህፃናት የልደትና የክትባት ምዝገባ ስርዓትን ከዲጂታል መታወቂያ ጋር ማስተሳሰር ወሳኝ መሆኑ ተነስቷል። የፋውንዴሽኑ ዋና መስራችና ስራ አስፈፃሚ ሰር ክሪስ ሆን ህፃናትን ከ 5 አመት እድሜ አንስቶ የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ውስጥ በማካተት መብትና ደህንነታቸውን ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት ኢትዮጵያ ፈር ቀዳጅ ሀገር መሆኗን ገልጸው አድናቆታቸውን ሰጥተዋል።
‎‎በቀጣይም እስከ ታችኛው መዋቅር የተቋቋሙ የሴቶች የልማት ህብረቶችን በማጠናከር፣ የህፃናት ፋይዳ መታወቂያ ምዝገባን፣ የልደት ምዝገባን፣ የክትባት ስራዎችን፣ የ CPIMS+ ስርዓትን እንዲሁም ለሴቶችና ህፃናት የሚሰጥ የፍትህ ስርዓትን ለማጠናከር በሚደረጉ ሁለገብ ስራዎች ላይ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል።
Please follow and like us: