የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር ከክብካቤ የሚወጡ ወጣቶችን በዘላቂነት ለማቋቋም የተጠናከረ ትብብር እንዲደረግ ጥሪ አቀረበ

በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር የሚኒስትሯ ልዩ አማካሪ ደበበ ባሩድ(ዶ/ር) “ከእንክብካቤ ወደ ፅኑ አቋም ለወጣቶች ቀጣይነት ያለው የሕይወት ጎዳና መገንባት” በሚል መሪ ቃል በተካሄደው ብሔራዊ የውይይት መድረክ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፣ መንግሥት ከአማራጭ እንክብካቤ ስርዓት ወጥተው ራሳቸውን ለመቻል የሚጥሩ ወጣቶችን ደህንነት ማረጋገጥ እንደ ዋና የልማት ስራ አይቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ወጣቶች በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፎች ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማስቻል ተስማሚ የፖሊሲ ማዕቀፎችን በመቀረጽ ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
ከኤስ ኦ ኤስ የሕፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ እና ከዴንማርክ መንግሥት ጋር በተደረገው አጋርነት ባስመዘገበው ውጤት አድናቆታቸውን ገልፀው ከአማራጭ ክብካቤ የመውጫ ዝግጅትና የድህረ ድጋፍ ዝቅተኛ መስፈርት መዘጋጀቱን፣ ወጣቶቹ በረቂቅ ብሔራዊ የወጣቶች ፖሊሲ ውስጥ እንዲካተቱ መደረጉን እና መረጃዎቻቸው በልዩ የዳታቤዝ ስርዓት (CPIMS+) እንዲያዙ መደረጉን አብራርተዋል።
ሆኖም አሁንም በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ከክብካቤ ወደ እራስን መቻል ሲሸጋገሩ የሥራ ዕድል፣ የመጠለያ እና ተቋማዊ የድጋፍ እጥረት የመሳሰሉ ተግዳሮቶች እያጋጠሟቸው መሆኑን አማካሪው ገልጸዋል።
በመሆኑም የመንግሥት መስሪያ ቤቶች፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ የግል ዘርፉ እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከዚህ ቀደም በበለጠ ተቀናጅተው በመስራት ወጣቶቹን የህብረተሰቡ የዕድገት ማዕዘን ድንጋይ እንዲሆኑ የማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
Please follow and like us: