ሚኒስቴሩ ከሰክሰስ ፕላስና ከክልሉ የሴቶች ወጣቶች ማኅበራዊ ጉዳይ ጋር በመተባበር የ5 ሚሊዮን ብር ዊልቸር ለአካል ጉዳተኞች ድጋፍ አደረገ።

ሚኒስቴሩ ከሰክሰስ ፕላስና ከአማራ ክልል የሴቶች ወጣቶች ማኅበራዊ ጉዳይ ጋር በመተባበር በደብረ ብርሃን ከተማ ለሚገኙ አካል ጉዳተኞች የ5 ሚሊዮን ብር ዊልቸር ድጋፍ አደርጓል።
‎በድጋፍ ርክክቡ ላይ የተገኙት የደብረ ብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት እንደተናገሩት፣ በከተማው አካል ጉዳተኞች በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተሰራው ሥራ ውጤታማ ነው ብለዋል። ‎​በተለይም አካል ጉዳተኞች ሰርተው ራሳቸውን እንዲችሉና እንዲለውጡ መስሪያና መሸጫ ቦታ በማመቻቸት፣ የመኖሪያ ቤት በመስጠት፣ ተደራጅተው የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ በማቅረብ እንዲሁም በቅርበት ክትትልና ድጋፍ በማድረግ በኩል ብዙዎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አመልክተዋል።
‎
‎​በዕለቱም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፣ የክልሉ ሴቶች ወጣቶች ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከበጎ አድራጎት ድርጅቱ ጋር በመተባበር የተደረገው ድጋፍ የመንቀሳቀስ ችግር ያለባቸውን ወገኖች ችግር ለመፍታት ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው በመጠቆም ምስጋና አቅርበዋል። ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ፍንጭ ሰጥተዋል።

‎‎የሰክሰስ ፕላስ የበጎ አድራጎት ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍሬውሁን መንገሻ በበኩላቸው፣ ድርጅቱ ባላፉት ሶስት ዓመታት በኢትዮጵያ በአራቱም አቅጣጫዎች ለአካል ጉዳተኞች ዘርፈ ብዙ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን አስታወቀዋል። ድርጅቱ በዋናነት በዊልቸር ድጋፍ፣ በገቢ ማስገኛ፣ በትምህርት ዕድልና ስፖንሰርሺፕ በመስጠት ከመንግስት ጋር በመተባበር እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ በደብረ ብርሃን ከተማ ለሚገኙ አካል ጉዳተኞችም 5 ሚሊዮን ብር ወጪ የሆነበት 100 ዊልቸር ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።
‎በአካል ጉዳተኞች ዘርፍ የሚታዩ የተሳሳቱ አመለካከቶችን ለማረም እና ሁለንተናዊ ተሳትፏቸውን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአካል ጉዳተኞች ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሲሳይ ጥላሁን አስታውሰው፣ ከለውጡ ወዲህ መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት ተሳትፏቸውን የሚያረጋግጡ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ አመልክተዋል። የአካል ድጋፍ መሳሪያዎች ዋጋቸው ውድ በመሆኑ በራሳቸው ገዝተው መጠቀም ለማይችሉ ወገኖች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፌዴሬሽኑ፣ ከሰርከስ ፕላስ እና ከአማራ ክልል ሴቶችና ማህበረሰብ ጉዳይ ቢሮ ጋር በመተባበር ድጋፍ ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል።
‎
‎የአማራ ክልል ሴቶች ወጣቶች ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ብርቱካን ሲሳይ እንደገለጹት፣ አካል ጉዳተኞች በማህበረሰቡ ዘንድ ባለው የተዛባ አመለካከት፣ የተደራሽነት እጥረት፣ የባለሙያና የተቋማት አሰራር ድክመቶች ምክንያት ለአካላዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተጋልጠው እንደሚገኙ ጠቁመዋል። በተለይም የእንቅስቃሴ ጉዳት ያለባቸው በርካታ ዜጎች በሰው ሰራሽ አካል ድጋፍ እጥረት ከቤት መውጣት አቅቷቸው እንደሚቸገሩ ጠቁመዋል።
‎
‎የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የአካል ጉዳተኞችን ችግር የሚቀርፉ የፖሊሲ ሀሳቦች ከማመንጨት ባለፈ፣ የተደነገጉ አለም አቀፍ ስምምነቶች በክልሉ ተፈፃሚ እንዲሆኑ እየሰራ እንደሚገኝ በመግለጽ፣ ተቋማዊ አሰራርን በማጠናከር፣ ልዩ አገልግሎቶችን በማስፋፋት፣ አካል ጉዳተኞችን በማብቃት ላይ ትኩረት መደረጉን ተናግረዋል።
‎
‎ድጋፍ የተደረገላቸው ወገኖች በተደረገላቸው ድጋፍ መደሰታቸውን በመግለጽ፣ የተሰጣቸውን ዊልቸር በአግባቡ ተጠቅመው እንደሚንቀሳቀሱ አመልክተዋል።

Please follow and like us: