ሚኒስቴሩ በአዲስ አበባ ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች እና ለመጠለያ ማዕከላት ዲጂታል የንፅህና መጠበቂያ ማከፋፈያ ማሽኖችን አስረከበ

ዲጂታል ማሽኖቹን የእቴጌ መነን የልጃገረዶች አዳሪ ት/ቤት እና ኮከበ ፅባህ ትምህርት ቤቶች የተረከቡ ሲሆን ከአዳማ፣ አዲስ አበባ እና ሲዳማ ክልል ለመጡና ለማህበራዊ ችግር ተጋላጭ የሆኑ ሴቶች መጠለያ ማዕከላት ማሽኖች መቅረባቸውን የሚያረጋግጥ የምስክር ወረቀትም ተሰጥቷል።

‎በመርሐግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፣ የወር አበባ የተፈጥሮ ስጦታ እንጂ የመገለል ምክንያት ሊሆን እንደማይገባ ገልጸው፣ የወር አበባ የንፅህና መጠበቂያ ተደራሽነትን ማስፋት የትውልድ ቀጣይነት እንዲሁም የሴቶች ክብርና የትምህርት መብትን የማረጋገጥ አካል መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል። ጉዳዩ በሴቶች ማጎልበት፣ በስርዓተ-ፆታ እኩልነት እና በትምህርት ፖሊሲዎች ውስጥ በብቃት መካተቱን በመግለጽ፣ ተማሪዎች ለትምህርታቸው ቅድሚያ እንዲሰጡ፣ የወላጆቻቸውንና የመምህራኖቻቸውን ምክር እንዲሰሙ እንዲሁም ከአሉታዊ የጓደኛ ተፅዕኖ እራሳቸውን እንዲጠብቁ አሳስበዋል።

“እምዬ” የተሰኘውን ዲጂታል ማከፋፈያ ማሽን ለአገልግሎት ያበቃውን የሴቶችና ልጃገረዶች ድጋፍ – ኢትዮጵያ ሀገር በቀል የበጎ አድራጎት ድርጅትን እና የገንዘብ ድጋፍ ያደረገውን UNFPAን ክብርት ሚኒስትሯ አመስግነዋል።
‎
‎የUNFPA ምክትል ተወካይ ሚስተር ታይዎ ኦሉዮሚን በበኩላቸው፣ ይህ ሀገራዊ ኢኒሼቲቭ ለታዳጊ ሴቶች የንፅህና መጠበቂያ በቀላሉ እንዲያገኙ፣ በተመጣጣኝ ዋጋና በጥራት እንዲቀርብላቸው ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል። አክለውም ይህ ፕሮጀክት ወደ ሌሎች አካባቢዎች ሊሰፋ የሚችል መሆኑን ጠቁመው፣ ድርጅታቸው ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር ያለውን አጋርነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በዘንድሮው አመት በአጠቃላይ 100 ዲጂታል ማሽኖችን ለማቅረብ ቃል የተገባ ሲሆን በትምህርት ቤቶችና በማዕከላቱ የሀይል መቆራረጥ በሚያጋጥምበት ወቅት የሶላር ሀይል ጥቅም ላይ እንዲውል የማሟላት ስራ እንደሚሰራ ተጠቁሟል። የትምህርት ቤቶቹ ዳይሬክተሮች ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል።

Please follow and like us: