ሴቶች ሲበረቱ፣ ሕፃናት ሲታነፁና ቤተሰብ ሲጠናከር ማኅበራዊ ብልጽግና እውን ይሆናል!

የሀገር እድገት የሚለካው በተገነቡ ተቋማትና በተመዘገቡ ስኬቶች ብቻ ሳይሆን፣ በዜጎች ሕይወት ላይ በሚያመጣው ለውጥ ጭምር ነው።
‎የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ መደመር ሐሳብ የጋራ አቅምንና ትብብርን የሚያጎላ ሲሆን፣ ከማኅበራዊ ልማት አንጻር ሲታይ የሴቶች ተሳትፎ፣ የሕፃናት ደኅንነትና የቤተሰቦች ጥንካሬ ለሀገር ብልጽግና መሠረታዊ መሆናቸውን እንገነዘባለን።
‎ሴቶች ዕድል ሲያገኙ፣ ተሳትፏቸው ሲያድግና አቅማቸውን ሲያሳዩ ድምፃቸው ይሰማል፣ ማኅበረሰቡም በሁሉም መስክ ይጠቀማል።
‎ሕፃናት ተገቢው ጥበቃና የተሟላ እንክብካቤ ሲያገኙና በትምህርት ታንፀው ሲያድጉ የነገ ሀገር ተረካቢዎች በትክክለኛ መሠረት ይገነባሉ።
‎ቤተሰብ የማህበረሰብ መሠረታዊ መነሻ እንደመሆኑ መጠን፥ ቤተሰቦች ሲጠናከሩና የተሻለ ኑሮ ሲኖራቸው በሂደቱ የሚጠቀመው ግለሰብ ብቻ ሳይሆን መላው ማኅበረሰቡ እና ሀገር ጭምር ናቸው።
‎የመደመር ማኅበራዊ ትርጉም የሚገለጠው ማንም ሰው ከልማት ዕድል ሳይገለል ሲቀር ነው። ምክንያቱም የሀገር እውነተኛ ብልጽግና የሚጀምረው ከሰው ልጅ ክብር፣ ደኅንነትና ተስፋ ነውና!
‎ማኅበራዊ ለውጥ የአንድ ተቋም ሃላፊነት ብቻ ሳይሆን የመንግሥት፣ የቤተሰብና የማኅበረሰብ የጋራ ጥረትና ድምር ውጤት ነው። የጋራ አቅምንና ትብብርን የሚያጎላው የመደመር እሳቤ በቃል የሚገለጽ አንድነት ብቻ ሳይሆን በተግባር የሚታይ ኃላፊነትና መደጋገፍን የሚጠይቅ በመሆኑ ለማህበራዊ አካታችነት፣ ለዜጎች የተሻለ ተጠቃሚነትና ለሀገራዊ ብልፅግና አብረን እንስራ።
Please follow and like us: