Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
በሰዎች የመነገድ ወንጀል ተጎጂ ለሆኑና ተጋላጭ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ፍልሰተኞች የሚደረግ ጥበቃና ድጋፍ ላይ ያተኮረ ስልጠና በባሕር ዳር ከተማ ተካሄደ
በሰዎች የመነገድና ሰዎችን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል ተጎጂ ለሆኑ እና በተጋላጭ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ፍልሰተኞች የሚደረግ ጥበቃና ድጋፍ ላይ ያተኮረ ሦስተኛ ዙር የአቅም ግንባታ ስልጠና በባሕር ዳር ከተማ ተካሄዷል።
ስልጠናው የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) ጋር በመተባበር፣ ከኔዘርላንድ መንግሥት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ እየተተገበረ ባለው ፕሮግራም አማካኝነች የተዘጋጀ ነው።
በሦስተኛው ዙር ስልጠና ከአማራ ክልል የተለያዩ ዞኖች የተውጣጡ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮዎች ባለሙያዎች ተሳትፈዋል። ስልጠናው በዋናነት በብሔራዊ የቅብብሎሽ ሥርዓት (National Referral Mechanism—NRM) አተገባበር ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ ተጎጂዎችንና በተጋላጭ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ፍልሰተኞችን በወቅቱና በተገቢው ለመለየት፣ የጥበቃ ፍላጎታቸውን ለመገምገም፣ ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር ትስስር ለመፍጠር እኝዲሁም ተገቢውንና የተቀናጀ የጥበቃና የድጋፍ አገልግሎት ማግኘታቸውን ለማረጋገጥ የበኩሉን አገዛ ያደርጋል።
ስልጠናው ዘላቂ ማኅበራዊ መልሶ ማቀላቀልን ማጠናከር ላይ የተሠማሩ ሙያተኞች በዘርፉ ያላቸውን ተግባራዊ እውቀትና ክህሎት ለማዳበር ያለመ ነው።
በክልልና በዞን ደረጃ የሚገኙ ባለሙያዎች የተጎጂዎችን መብት፣ ክብርና ደህንነት በማስጠበቅ፣ የተቀናጀ፣ ተደራሽና ተጎጂ ተኮር የጥበቃና የድጋፍ ሥርዓትን በተግባር እንዲያስፈጽሙ አቅማቸውን የማጠናከር ሥራ በቀጣይነት እንደሚከናወን ተጠቁሟል።
