የአየር ንብረት ለውጥ በሴቶች ላይ የሚያደርሰውን ተጽእኖ በመከላከል እንዲሁም የስረአተ ጾታ እኩልነት በተመለከተ የውይይት መድረክ ተካሄደ

በመጋቢት ወር 2014 ዓ.ም የአየር ንብረት ለውጥ በሴቶች ላይ የሚያደርሰውን ተጽእኖ በመከላከል እንዲሁም የስረአተ ጾታ እኩልነትና ሴቶች በዚህ ሂደት በሚኖራቸው ሚና ላይ ትኩረት አድርጎ በኒውዮርክ ከተማ ለሚካሄደው የስልሳ ስድስተኛው የተባበሩት መንግስታት ኮሚሽን ስብሰባ (The sixty-sixth session of the UN Commission on the Status of Women (CSW66) የአፍሪካ ሴቶች የጋራ አቋም ለማያዝ የሚያስችል የውይይት መድረክ በአፍሪካ ህብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሄዷል፡፡
የውይይት መድረኩን በይፋ ያስጀመሩት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ክብርት ሳህለወርቅ ዘውዴ ባስተላለፉት መልእክት የአፍሪካ ሴቶችን የመሪነት ሚና እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን በተለያዩ የስራ ፈጠራ መስኮች በማሰደግ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል የገለጹ ሲሆን በሴቶች ሁሉ አቀፍ ተጠቃሚነት ላይ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
የውይይት መድረኩ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ሚኒስትሮች በአካልና በቪዲዮ ኮንፍረንስ የተሳተፉ ሲሆን በሶስት ወሳኝ አጀንዳወች ላይ ማለትም የአየር ንብረት ለውጥ በሴቶች ላይ የሚያደርሰውን ተጽእኖ በመከላከል ረገድ መከናወን በሚገባቸው ጉዳይ ላይ ውይይት ተደርጎ ስምምነት ላይ ተደርሷል፣ በተጓዳኝ አደጋዎችን መከላከልና አቀም መፍጠር የሚችሉ ፖሊሲዎችን፣ ፕሮግራሞችና መልካም ተመኩሮዎችን ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታና በቀጣይ ወር በሴቶች ላይ ትኩረት አድርጎ በኒውዮርክ ለሚካሄደው የስልሳ ስድስተኛው የተባበሩት መንግስታት ኮሚሽን ስብሰባ የአፍሪካ ሴቶች ዋና ዋና መልእክቶች ላይ የጋራ አቋም መያዝ ተችሏል፡፡
በተመሳሳይ የዚሁ ወይይት ክፍል የሆነው በስረአተ ጾታ እኩልነትና ሴቶችን በማብቃት ላይ ትኩረት ያደረገው 6ኛው ስፔሻላይዝድ ቴክኒካል ኮሚቴ ውይይት ጾታዊ ጥቃትን በማስቆም የወንዶችን ሚናና አዎንታዊ ተጸእኖ ማጠናከር እንዲሁም የአፍሪካ ሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ሊያጎለብት በሚችሉ ጉዳዮችና የስረአተ ጾታ እኩልንትን ለማረጋገጥ እ.አ.አ በ2004 የሶሌመን ዲክላሬሽን ተብሎ የሚጠራውን ስምምነትን መሰረት ተደርጎ የተከናወኑ ስራዎች በተመለከተ የአፍሪካ ሪፖርት ቀርቦ ጸድቋል፡፡
በእለቱም በመድረኩ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው እንደገለጹት በኢትዮጵያ ተቀርጸው እየተተገበሩ የሚገኙ ፖሊሲዎች፣ፕረግራሞችና እቅዶች በአለም አቀፍ ደረጃ የጸደቀውን የቤጂንግ ስምምነትና እሱን ተከትሎ የተተገበረውን ሴቶችን የማብቃት እንዲሁም የስረአተ ጾታ እኩልነትን የማካተት አጀንዳን እንደ ዋና ቁልፍ መነሻ አድርጎ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም እንደ ሀገር የተተገበሩ ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞች ቀጣይነት ያለውን እድገት ለማምጣት የተተለመውን የ2030 አጀንዳና “የምንመኛት አፍሪካ” በሚል ራእይ እየተተገበረ ያለውን የ2063 አጀንዳን መሰረት ያደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በመጨረሻም በስብሰባው ላይ የተካፈሉትና ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የመጡ ሚኒስትሮችና የተለያዩ አለም አቀፍ ድርጅት ተወካዮች የወዳጅነት ፓርክን በመጎብኘት የሀገራችንን መልካም ገጽታና በጎ ጅማሮ አድንቀዋል፡፡
Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *