ኢትዮጵያና ሞሮኮ ሴቶችን በኢኮኖሚና በክህሎት ብቁ ለማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመስራት ተስማሙ

ኢትዮጵያና ሞሮኮ ሴቶችን በኢኮኖሚና በክህሎት ብቁ ለማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመስራት ተስማሙ፡፡ ይህ የተገለጸው የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ከኢትዮጵያ የሞሮኮ አምባሳደር ከሆኑት ኔዝሃ አላኢ ጋር በጽህፈት ቤታቸው በተወያዩበት ወቅት ነው፡፡
በውይይታቸው ወቀት ክብርት አምባሳደሯ እንደገለጹት ሞሮኮ በኢትዮጵያ በተለይም የገጠር ሴቶችን ማእከል ያደረገ የግብርና ምርታማነትን በሚጨምሩ ክህሎቶች ዙሪያ፣የሴቶችን የኢኮኖሚ አቅምና የሙያ ክህሎት የሚያጎለብቱ ልምዶችን እንዲሁም ሴቶችን ታሳቢ ያደረጉ የብድርና ቁጠባ ህብረት ስራ ማህበራትን በአሰራር ማዘመን በሚቻልበት ሂደት ላይ ያላቸውን ልምድ ማካፈል እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡
ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው እንደገለጹት ሴቶችን በኢኮኖሚ፣በትምህርትና በክህሎት ማጎልበቻ ስልጠና አምራችና በቁ ዜጋ እንዲሆኑ እንደ ሀገር ለተጀመረው ሁሉ አቀፍ ጥረት ሞሮኮ ያላት ልምድ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው በዘርፉ ውጤታማ ለመሆን አብሮ መስራቱ እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ በውይይታቸው ላይ ኢትዮጵያና ሞሮኮ የሴቶችን ኢኮኖሚ ለማሳደግና የጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ በሚከናወኑ ተግባራት ላይ ተቀራርቦ ለመስራትና እንደ ሀገር ኢኮኖሚያዊ ለውጥን ለማምጣት በሚያስችሉ የሁለትዮሽ ትብብር በዋናነት “south-south cooperation” ለማጠናከር ተስማምተዋል፡፡
Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *