አለም አቀፍ የሴቶች ቀን የማጠቃለያ መርሃ ግብር

የሴቶችን መብቶች ከመጠየቅና ከማስከበር አኳያ ቀደምትና ለሌሎች ዓለማት ተምሳሌት የሚያደርጉን በርካታ ታሪኮች እንዳሉን ልናስተውል ይገባል
አለም አቀፍ የሴቶች ቀን የማጠቃለያ መርሃ ግብር ላይ በመገኘት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደገለጹት የሴቶችን መብቶች ከመጠየቅና ከማስከበር አኳያ ቀደምትና ለሌሎች ዓለማት ተምሳሌት የሚያደርገን በርካታ ታሪኮች እንዳሉን ልናስተውል ይገባል፡፡
በሴቶች ላይ የሚደርሰውን የባህል ተፅዕኖና የወንዶች የበላይነትን በመቃወም ከአስር በላይ የመብት ጥያቄዎችን ይዛ የታገለችውንና ለስኬት የበቃችውን የቃቄ ወርድወት የተባለችውን የለውጥ አርበኛ ታሪክ ታሪክ የጠቀሱት ሚኒስትሯ የዚህችን ጀግኒት ሴት እውነተኛ ታሪክ መዘከርና በወቅቱ የነበረውን ለትውልድ ማስተላለፍ ጠቃሚና አስተማሪ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አለም አቀፍ የሴቶችን ቀን ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው ሃገር አቀፍ ንቅናቄ የድርጊት መርሃ ግብር ከየካቲት 1 እስከ መጋቢት 18 ቀን 2014 ዓ.ም በማህበራዊ ጉዳይ በሰው ሰራሽ እና በተፈጥሮ አደጋዎች ተጎጂ የሆኑ ሴቶች እና ህፃናት ሁለንተናዊ ድጋፎችን እንዲያገኙ የሀብት ማሰባሰብ ተግባር በመስራት በዘላቂነት ከችግር እንዲወጡ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ችግር ለደረሰባቸው ሴቶችና ህፃናት የስነ-ልቦና ድጋፍ አገልግሎት /psycho-social training / በመስጠት ወደ ቀድሞ ህይወታቸው እንዲመለሱ ከማድረግ በተጓዳኝ ጥቃት የደረሳባችው ሴቶች ምላሽ አሰጣጥና አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን የማጠናከር ስራ ከመሰራት በተጨማሪ በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች የሴቶች ህብረት ስራ ማህበራት የማጠናከርና የተሻለ አፈፃፀም ያላቸውን ማህበራት እውቅና እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ሃገር አቀፍ ንቅናቄው የሴት አደረጃጀቶችና የልማት ቡድኖችን የበለጠ ለማጠናከርና ለማቋቋም እድል ከመፍጠር ባሻገር የሴቶች ልማት ቡድን ለአካባቢያቸው ሰላም ግንባታና በብሄራዊ ደረጃ በተዘጋጀው የምክክር መድረክ ጉልህ ሚና እንዲጫወቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
”እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ !!! ” የሚለው መሪ ቃል የተመረጠበት ዋናው ዓላማ አስመልክተውም በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በማስቆም ህብረተሰቡ የወንጀል ድርጊቱን እንዲጸየፍና ፈጻሚዎችን በማጋለጥና ለፍትህ ለማቅረብ የሚያስችል መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ላይ የአመለካከት ለውጥ ለማምጣትና በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ለተጋለጡ ወገኖቻችን የጋራ የሆነ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በጋራ መረባረብ፣ በባለቤትነትና በቅንጅት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በመጨረሻም በሃገራችን በተከሰተው የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ቤት ንብረታቸው የወደመባቸውና የተፈናቀሉ ዜጎቻችን ቁጥር በርካታ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ አጋር አካላትንና ህብረተሰቡን በማሳተፍ ድጋፍ በማሰባስብ በአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ተቋማት፣ በተሃድሶ ማዕከላትና ተፈናቃይ ወገኖቻችን በሚገኙበት ስፍራ ሁሉ በመገኘት ላበረከቱት አስተዋጽዖ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የዘንድሮውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ” እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ !!! ” በሚል መሪ ቃል በዓለም አቀፍ ለ11ኛ ጊዜ በሃገራችን ደግሞ ለ46ኛ ጊዜ የተከበረ ሲሆን የበዓሉ ዋና ዓላማ በሃገራችን ለሴቶች እኩልነት የተደረገውን ትግልና ውጤት ከመዘከር ባሻገር ሴቶች በየደረጃው በሚካሄዱ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎች ላይ በንቃት በመሳተፍ የላቀ ስኬት ለማስመዝገብና ሴቶች የራሳቸውን ታሪካዊ አሻራ ማሳረፍ እንዲችሉ ማነሳሳትና ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነው፡፡
Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published.