Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ሴቶች የስነ ልቦናና የንግድ ክህሎት ስልጠና ተጀመረ
በሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞኖች በጦርነቱ ምክንያት የስነልቦና፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት የደረሰባቸው ሴቶች ተገቢው የስነልቦና፣ ማህበራዊ ድጋፍ እና የስራ እድል መፍጠሪያ የሚሆን መሰረታዊ የንግድ ክህሎት ስልጠና በደሴና በወልዲያ ከተሞች 150 ለሚሆኑ ሴቶች ስልጠና መስጠት ተጀምሯል።
በስልጠናው መከፈቻ ፕሮግራም ላይ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶችና ህፃናት ጉዳዮች ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ ክብርት ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ እንደገለጹት ሚኒስቴር መ/ቤቱ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ ሲሆን የዚህ ድጋፍ አካል የሆነው በአማራ ክልል በሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞኖች ለተለያዩ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ለደረሰባቸው ሴቶች በተዘጋጀው ስልጠና የሚሳተፉ ሰልጣኞች በስልጠናው የሚያገኙትን እውቀትና ክህሎት ተጠቅመው በተለያዩ የስራ መስኮች በራሳቸው ፍላጎት ተሰማርተው ችግርን ተቋቁሞ ውጤታማ በመሆን ለሌሎችም አርአያ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ገልፀዋል፡፡
በመክፈቻና በፊርማ ፕሮግራሙ ላይ የአማራ ክልል ሴቶች፤ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ብርቱካን ሲሳይ፣ የደሴ ከተማ የሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ሀላፊ ወ/ሮ ምሳዬ ከድር፣ የሰሜን ወሎ ዞን የሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ደስታ አራጋው፣ የደቡብ ወሎ ዞን የሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ የወ/ሮ ቤተልሄም ብርሃኑ ተገኝተው በተመሳሳይ ለሰልጣኞች የማነቃቅያ ንግግር አድርገዋል፡፡
በስልጠናው የስነልቦናና የማህበራዊ ድጋፍ ከመስጠት ባሻገር የስራ እድል መፍጠሪያ የሚሆን የ5 ቀን የንግድ ክህሎት ስልጠና የሚሰጣቸው ሲሆን ከስልጠናው በኃላ የስራ ማስጀመሪያ የሚሆን በመንግስት በተመደበ በጀት መነሻ ካፒታል ለእያንዳንዳቸው የሚሰጥ ሲሆን ይህንን ስራ በቅንጅት ለመስራት እንዲያስችል በሚኒስቴር መ/ቤቱና በአማራ ክልል ሴቶች፣ ህጸናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ እንዲሁም ክልሉ ከሰሜን ወሎ እና ከደቡብ ወሎ ዞን የሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ መካከል የውል ስምምነት እንዲፈጸም ተደርጓል፡፡
Please follow and like us:
