ለተቋሙ የጽህፈት፣ የቢሮ አስተዳደርና የጥበቃ አገልግሎት ባለሙያዎች የተዘጋጀው 2ኛው ዙር ስልጠና ተካሄደ፡፡

የተገልጋይ እርካታን የላቀ ደረጃ ላይ ለማድረስ የፈጻሚዎችን አቅም በዘላቂነት ለማጎልበት በተዘጋጀው በዚህ የምልክት ቋንቋ የክህሎት ስልጠና መርሃ ግብር መክፈቻ ላይ በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ መሪ ስራ አስፈጻሚ ተወካይ አቶ ሲሳይ ጥላሁን እንደገለጹት ወደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚመጡ መስማት የተሳናቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች አካታች የሆነ አገልግሎት ለመስጠት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በመሰጠት ላይ የሚገኘው የምልክት ቋንቋ ስልጠና በሌሎችም የመንግስት አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች ትኩረት ሊያገኝና ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡
የህብረተሰቡ አንድ አካል የሆኑትን አካል ጉዳተኞችን በእኩልነት መርህ ማገልገል በአለም አቀፍና በሃገራችን በወጡ የተለያዩ የህግ ማዕቀፎች ውስጥ የተደነገገ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሲሳይ ጥላሁን የአካል ጉዳተኞችን ሰብዓዊ መብቶች በማክበርና በማስከበር መስማት የተሳናቸው ወገኖቻችን መግባቢያ የሆነውን የምልክት ቋንቋ ማወቅ አካታችና ተደራሽነት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ጉልህ አስተዋጽዖ አለው ብለዋል፡፡
የስልጠናው አስተባባሪ አቶ አለማየሁ ማሞ በበኩላቸው ከየስራ ክፍሉ የተወጣጡ የጽህፈት፣ የቢሮ አስተዳደርና የጥበቃ አገልግሎት ባለሙያዎች በምልክት ቋንቋ ማሰልጠን ያስፈለገው የተገልጋዮች እርካታ የሚጀምረው ከእነዚህ የስራ ክፍሎች መሆኑን ጠቅሰው “ከፍትፍቱ ፊቱ” እንዲሉ መስማት የተሳናቸው ተገልጋዮች በየትኛውም ተቋም ከጥበቃ አገልግሎት ጀምሮ በየደረጃው የሚሰጠውን አገልግሎት ተቋማዊ ይዘት እንዲኖረው ትኩረት ሰጥቶ መስራትና ተሞክሮውን በሁሉም መንግስታዊ ተቋማት ማስፋት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
የስልጠናው ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት የምልክት ቋንቋ ስልጠናው የአገልግሎት አሰጣጣቸውን ለማሻሻል፣ የአገልጋይና ተገልጋዮችን ግንኙነት የተቃና ለማድረግና በተግባቦት ዘርፍ የነበረውን ክፍተት ለመሙላት ጉልህ ድርሻ እንደነበረው ገልጸው ይህን መሰሉ ስልጠና ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ለሌሎች የስራ አጋሮቻቸው እንዲዳረስ የስራ አስፈጻሚ ጽ/ቤቱ ተገቢውን ጥረት እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡
Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *