አለም አቀፍ የሴቶች ቀንን – ማርች 8ን አስመልክቶ የዜና መግለጫ

በቅድሚያ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የበዓሉ ባለቤት ለሆኑት የአገራችን ሴቶች በሙሉ ለዘንድሮው አለም አቀፍ የሴቶች ቀን ወይም ማርች 8 በዓል እንኳን በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን እያለ መልካም ምኞቱን ይገልጻል፡፡

እንደሚታወቀው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በዋነኝነት ሴቶች ለፍትህና ለእኩልነት ያደረጉትን መራር ትግልና የተገኘውን ውጤት ከመዘከር ባሻገር ሴቶች በሚካሄዱ የልማት እንቅስቃሴዎች ላይ በንቃት በመሳተፍ የላቀ ስኬት ለማስመዝገብና ታሪክ ለመስራት የበለጠ እንዲነሳሱና ከሚገኘውም ትሩፋት እኩል ተቋዳሽ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ዓላማን ሰንቆ በየአመቱ የሚከበር ታላቅ አለም አቀፍ ኩነት ነው፡፡

በዓሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በየአመቱ የሚቀርጻቸውን መሪ ሃሳቦች መሰረት በማድረግ እንደየአባል ሀገራቱ ተጨባጭ ሁኔታ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች እየተከበረ የሚገኝ ሲሆን ዘንድሮም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ112ኛ ጊዜ “Digit ALL: Innovation and technology for gender equality.” ”ፈጠራ እና ቴክኖሎጂ ለጾታ እኩልነት” በሚል መሪ ቃል በሀገራችን ደግሞ “እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ” በሚል መሪ ቃል ለ47ኛ ጊዜ ከየካቲት 20 ጀምሮ በልዩ ልዩ የንቅናቄ መርሀ ግብሮች እየተከበረ ይገኛል፡፡

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የዘንድሮው አለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ ከተለያዩ ባለድርሻና አጋር አካላት ጋር በመተባበር በዋነኝነት በሰላም፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በመከላከልና በማስቆም ረገድ በተከናወኑ ተግባራትና በተገኙ ውጤቶች ዙሪያ የመስክ ጉብኝትና የተሞክሮ ልምድ ልውውጥ ማካሄድ፣ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ አቅም ማሳደግ፣ የወንዶችን አጋርነት ማጠናከር እንዲሁም ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖችና ማህበራዊ አገልግሎት ለሚሰጡ ተቋማት ልዩ ልዩ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች፣ የምግብ ግብዓቶችና አልባሳትን ድጋፍ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ትኩረት በማድረግና በሌሎችም እንደአገር በተመረጡ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ አጀንዳዎችን በመቅረጽ ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ወጥ በሆነ መልኩ የሴቶች ተሳትፎ ለማሳደግና የህብረሰተቡን አመለካከት ለመለወጥ የሚያግዙ ሰፋፊ የግንዛቤና ንቅናቄ ስራዎችን እያካሄደ ይገኛል፡

በተለይም በአሁኑ ወቅት አገራችን ባጋጠማት በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ችግሮች በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች በተከሰቱት ግጭትና ድርቅ ምክንያት የተጎሳቆሉ ዜጎቻችንን በመታደግና ወደ ዘላቂ ሰላም እንዲመለሱ የእርቅ፤ የመረዳዳትና የመደጋገፍ ሂደት ላይ ሴቶች እጅግ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን በተጨባጭ ስንረዳ እለቱን ከምንጊዜውም በላይ ማክበር ትርጉም ይኖረዋል፡፡ በመሆኑም የንቅናቄ መርሀ ግብሩ እስከ መጋቢት 20 ቀን 2015 ዓ.ም የሚቀጥል ይሆናል፡፡

ኩነቱ በዋነኝነት “እኔ እህቴ ጠባቂ ነኝ” በሚል በመሪ ቃል በዓሉ መከበሩ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች፣ ማናቸውም ጾታዊ ጥቃቶች እንዲሁም እንደሰላም እጦት ባሉ ሰው ሰራሽና ሌሎች ተፈጥሯዊ ክስተቶች ሳቢያ ሴቶች፣ ታዳጊ ልጃገረዶችና ህጻናት ግንባር ቀደም ተጎጂዎች በመሆናቸውና ይህም የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ጨምሮ ለአካላዊ፣ አእምሯዊ፣ ስነልቦናዊ ጉዳት ብሎም ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንዲጋለጡ ስለሚያደርግ መብታቸውን ለማስከበር፣ የእኩልነት መርህን መሰረት ባደረገ መልኩ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸውን ለማስጠበቅ ችግሮቻቸውን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እንደሀገር እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ውጤት እንዲያስገኙ ሁሉም በእኔነትና በባለቤትነት ስሜት በመነሳሳት እንዲረባረብ፣ ተግባራዊ ምላሽ እንዲሰጥና ማህበራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ የሚያስችል የማህበረሰብ ንቅናቄ መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡

ስለሆነም የእናቱ፣ የእህቱ አሊያም የሴት ልጁ ጉዳይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የማይመለከተው ግለሰብ፣ ዜጋና ማህበረሰብ ስለሌለ የሴቶችን ህይወት የሚጎዱ፤ ሁለንተናዊ ተሳትፎኣቸውንም ሆነ ተጠቃሚነታቸውን የሚገቱና የወደፊት ተስፋቸውን የሚያጨልሙ የተሳሳቱ አመለካከቶችንና ድርጊቶችን በመታገል ከምንጩ ለማድረቅ ወንዶችን ጨምሮ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ህብረተሰቡ ሌሎች የልማት አጋራትም ከጎናቸው እንዲቆምና በተጨባጭም አጋርነቱን እንዲያሳያቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *