በቤኒሻንጉል ክልል በፀጥታ ችግር ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሚሰጡ የስነልቦና፣ ማህበራዊና የአዕምሮ ጤና ድጋፍ አገልግሎቶችን ውጤታማነት ለማሳደግ የሚያስችል ስልጠና እየተሰጠ ይገኛ

(አሶሳ፣ መጋቢት 10/2015 ዓ.ም) የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በቤኒሻንጉል ክልል በፀጥታ ችግር ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች በተለያዩ ባለድርሻ አካላት የሚሰጡ የስነልቦና፣ ማህበራዊና የአዕምሮ ጤና ድጋፍ አገልግሎቶችን ውጤታማነት ለማሳደግ የሚያስችል የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል።

የስልጠና መርሀ ግብሩን ያስጀመሩት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚኒስትር ፅህፈት ቤት ኋላፊ ወ/ሮ እታገኝ አሰፋ እንደተናገሩት፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና ከጤና ሚኒስቴር፣ ከተባበሩት መንግስታት የህፃናት አድን ድርጅት /ዩኒሴፍ/፣ ከሚመለከታቸው የክልል አስፈፃሚ አካላት እና ከተለያዩ የሙያ ማህበራት ጋር በመቀናጀት በሀገራችን ባለፉት ዓመታት በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ክስተቶች ሳቢያ በግለሰብና በማህበረሰብ ላይ የደረሰውን የስነልቦና፣ ማህበራዊና የአዕምሮ ጤና ችግሮች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት የሚያስችል የጋራ እቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር መገባቱን አስታውሰዋል።

ጉዳት ለደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በእውቀት ላይ የተመሰረተ፣ ፈጣን፣ ቀልጣፋና የተቀናጀ ተግባራዊ የድጋፍ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ተቋማዊ አሰራር መዘርጋት አስፈላጊ በመሆኑ በተለያዩ ጊዜያት ችግሩ በተከሰተባቸው የአማራ፣ አፋርና ሌሎችም አካባቢዎች ለሚገኙ የማህበራዊ ሴክተር ባለሙያዎችና የማህበረሰብ ተወካዮች ስልጠና ሲሰጥ መቆየቱን ገልፀዋል።

በቤኒሻንጉል ክልል እየተሰጠ ያለው ስልጠናም የእቅዱ አካል መሆኑን የጠቆሙት ኋላፊዋ ሰልጣኞች የቀሰሙት እውቀት ወደታች እንዲያወርዱ፣ ለሌሎች እንዲያካፍሉና በአግባቡ በስራ ላይ በማዋል ማህበረሰባቸውን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ አፅዕኖት ሰጥተው አሳስበዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቀጣይም የተቀናጀ ተግባራዊ ምላሽ በመስጠት፣ የተቋማትን አቅም በመገንባት ረገድ እንዲሁም የተጎዱ ወገኖች ከጉዳታቸው እንዲያገግሙና በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ለማስቻል የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ለፕሮጀክቱ ስኬታማ ትግበራ የተባበሩ አካላትን በተጠቃሚ ወገኖች ስም አመስግነው፤ ሆኖም ከችግሩ ስፋት አኳያ አሁንም ብዙ መስራት የሚጠይቅ በመሆኑ ድጋፋቸው ቀጣይነት እንዲኖረው ኋላፊዋ ወ/ሮ እታገኝ አሰፋ ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት የመልሶ ማቋቋምና ሪዜሊያንስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ያረጋል ፉፋ በበኩላቸው ስልጠናው በዋነኝነት በአዕምሮ ጤና፣ በፆታዊ ጥቃት መከላከልና ምላሽ አሰጣጥ፣ በማህበረ- ስነልቦናዊ ድጋፍ፣ በህፃናት ጉዳይ አያያዝና ተያያዠ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ተናግረዋል። ከስልጠናው በተጨማሪ ለጉዳት ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰሰብ ክፍሎችን በዘላቂነት ለማቋቋምና ህይወታቸውን ለመታደግ ሚኒስቴሩ ወደፊትም ቅንጅት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

ስልጠናው በክልሉ ለተጀመሩ የድህረ ጦርነት ስራዎች መሳካት የበኩሉን እገዛ እንደሚያደርግ የገለፁት የክልሉ መስተዳደር የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ አቶ ጌታቸው ፊሊጶስ፤ የተፈለገው ውጤት እንዲመጣም በየደረጃው በየዘርፉ ያሉ የክልሉ አመራሮችና ባለሙያዎች ከማህበረሰብ አደረጃጀቶች እንዲሁም ከባለድርሻና አጋር አካላት ጋር ተቀናጅተው እንዲረባረቡና ኋላፊነታቸውን እንዲወጡ አያይዘው መልዕክት አስተላልፈዋል።

በስልጠና መርሀ ግብሩ ከትምህርት፣ ከጤናና ከፍትህ ሴክተር እንዲሁም ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች የተውጣጡ እና ሌሎችም በማህበራዊ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ በድምሩ 300 ሰልጣኞች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *