በኦሮሚያ ክልል በግጭትና ሰው ሰራሽ ክስተቶች ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የተቀናጀ ድጋፍ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ለባለሙያዎች እየተሰጠ ይገኛል።

(አዳማ፣ መጋቢት 29/ 2015 ዓ.ም) በኦሮሚያ ክልል በግጭትና ሰው ሰራሽ ክስተቶች ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የተቀናጀ ድጋፍ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ለባለሙያዎች እየተሰጠ ይገኛል።

በስልጠና መርሀ ግብሩ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አየለች እሸቴ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለፁት፤ መንግስት በሀገራችን በተለያዩ ጊዜያት በግጭትና ሰው ሰራሽ ክስተቶች ምክንያት በግለሰብና በማህበረሰብ ለተፈጠረ የአዕምሮ ጤና፣ የስነልቦናና የማህበራዊ ችግር ምላሽ ለመስጠት፣ ተጎጂዎችን ለመደገፍና መልሶ ለማቋቋም የአምስት አመት ፕሮጀክት ነድፎ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ከጤና ሚኒስቴር፣ ከክልሎችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ከዩኒሴፍና ከአለም ባንክ በተገኘ ድጋፍ የጋራ እቅድ በማዘጋጀት፣ የተቋማትንና የአስፈፃሚ አካላትን የማስፈፀም አቅም ለማጎልበት የሚያግዙ ተግባባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል።

ስልጠናው የእቅዱ አካል መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ በዘርፉ የሚታየውን የእውቀትና የክህሎት ክፍተት በመቅረፍ የተቀናጀና በእውቀት ላይ የተመሠረተ የድጋፍ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ተቋማዊ አቅም ለመፍጠር ያለመ እንደሆነም አያይዘው ገልጸዋል።

የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናው በዋነኛነትም በጾታዊ ጥቃት ምላሽ አሰጣጥ፣ በአዕምሮ ጤና፣ በማህበራዊና ስነልቦናዊ ድጋፍ እንዲሁም በህጻናት ጉዳይ አያያዝ ላይ ያተኮረ መሆኑ ተጠቁሟል።

ከዚህ ቀደም ስልጠናው በአማራ፣ በአፋር፣ በቤኒሻሻንጉል ጉምዝና በኦሮሚያ ክልሎች በተመሳሳይ መልኩ መሰጠቱ ይታወሳል።

በጤና ሚኒስቴር የጤና አገልግሎት እና ፕሮግራም ዘርፍ አማካሪ አቶ ኢዶሳ አዱኛ በበኩላቸው እንደሀገር በግለሰብና በማህበረሰብ ደረጃ ከአዕምሮ ጤናና ከስነልቦና ጋር በተያያዘ የተከሰቱ ችግሮችን ለመቅረፍና በዘርፉ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ሁሉም ሊረባረብ እንደሚገባ አሳስበዋል። ባለሙያዎችም የወሰዱትን ስልጠና በስራ ላይ ማዋል ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። የጤና አገልግሎቶችና ፕሮግራሞች ተደራሽ እንዲሆኑም ተገቢው ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግም አስታውቀዋል።

በስልጠና መርሀ ግብሩ ከኦሮሚያ ክልል ከተለያዩ ዞኖች ከትምህርትና ከጤና ሴክተር የተውጣጡ ከ300 በላይ ባለሙያዎች፣ የማህበራዊ ዘርፍ ሰራተኞችና ተፅዕኖ ፈጣሪ አካላት እየተሳተፉ እንደሚገኙ የገለጹት የክልሉ የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ጀሚላ ስንብሮ ናቸው።

በዕለቱ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተቀርፆ በአለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ እየተተገበረ የሚገኘውና ጉዳት ለደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ምላሽ ከመስጠት፣ እንዲያገግሙ ከማድረግና በዘላቂነት ከማቋቋም አኳያ የ3R ወይም (Response, Rehabitation & Resilence) ኘሮጀክት የትግበራ ሂደት በተመለከተ አስተባባሪው አቶ ወንድሙ ዱታሞ አብራርተዋል።

Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *