ሴቶች ለሰላም መከበር አበክረን መስራት አለብን – ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሁሪያ አሊ

“የኢትዮጵያን ሰላም እጠብቃለሁ፤ ለልጆቼ ምንዳን አወርሳለሁ” በሚል መሪ ሃሳብ ሴቶች በሰላም ዙሪያ የሚያበረክቱትን አስተዋፅኦ የዳሰሰ የውይይት መድረክ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።

በውይይቱ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ እንደገለፁት ሴቶች ለሰላም መከበር አበክረን መስራት አለብን ሲሉ ገለጹ። ሚኒስትር ዴኤታዋ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የተለመችውን የእድገትና ብልጽግና ጉዞ ዳር ለማድረስ ሰላም መከበር አለበት። ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት የአገራችን መዳረሻ የሆነውን ብልጽግና ለማረጋገጥ መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራም እንደሚገኝ ገልጸዋል ።ለዚህም ከ50 በመቶ በላይ የሆኑት ሴቶች ለሰላም አበክረን በመስራት ከመንግስት ጎን መቆም አለብን ሲሉም ገልጸዋል።

በተጨማሪም በውይይቱ የተገኙት የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር ወይዘሮ ባንችአምላክ ገብረማርያም በበኩላቸው፤ በክልሉ የተሟላ ሰላም ይሰፍን ዘንድ በትብብር መስራት ይገባናል ብለዋል። በየዘርፉ የተሰማራው ሁሉ ውጤታማ ስራዎችን ማከናወን እንዲችል ዋነኛ መሳሪያ የሆነውን ሰላም ለማረጋገጥ ሴቶች በጋራ ልንቆም ይገባል ሲሉም ተናግረዋል። በውይይቱ የተሳተፉ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው በህይወት ለመኖርና ሰርቶ ለማደር ሰላም ወሳኝና አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

የሰላም መታጣት በህብረተሰቡ የዕለት ከዕለት ኑሮ ላይ ጫና እንደሚያሳደር ጠቅሰው፤ ዘላቂ ሰላም ለማስፈንም ሴቶች በሰላም ማስፈን ላይ በማተኮር ልንሰራ ይገባል ብለዋል። አሁን ላይ ያጋጠሙንን ችግሮች ለመፍታት እንደዚህ አይነት ውይይት መዘጋጀቱ አስፈላጊ ነው ሲሉም የውይይቱ ተሳታፊዎች ገልፀዋል።በሰላምና ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ባተኮረው ዉይይት ላይ በባህርዳር ከተማ ከሁሉም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ ሴቶች ተሳታፊ ሆነዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

Please follow and like us: