የወጣት ሴቶችን የዲፕሎማሲ ተሳትፎ ለማበረታታት በትኩረት መስራት ይገባል – ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

የወጣት ሴቶችን የዲፕሎማሲ ተሳትፎ ለማበረታታት በትኩረት መስራት እንደሚገባ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ። ፕሬዝዳንቷ ይህን ያሉት ሁለተኛው “የሴቶች በዲፕሎማሲ ዓለም አቀፍ ቀንን” አስመልክቶ በተዘጋጀ መርሀ ግብር ላይ ነው።

ኢትዮጵያ የወጣት ሴቶችን የዲፕሎማሲ ተሳትፎ ለመጨመር ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሜንተርሺፕ በመስጠት እያከናወነ ያለውን ተግባር ፕሬዝዳንቷ አንስተዋል። እስካሁን ባለውም 1 ሺህ 500 ወጣት ተማሪዎች መርሀ ግብሩን መከታተላቸውን ጠቅሰዋል።በመሆኑም በአህጉር እንዲሁም በአገር ደረጃ ወጣት ሴት ዲፕሎማቶችን ተሳትፎ ለመጨመርና ለማበረታታት በትብብር መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል። በሌላ በኩል ሴቶች በሰላምና ጸጥታ እንዲሁም ግጭት አፈታት ያላቸውን ተሳትፎ ለመጨመር በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል ፕሬዝዳንቷ።

የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ፀሐፊ ክላቨር ጋቴቴ በበኩላቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ሴቶች በአምባሳደርነት፣ በውጭ ጉዳይና ሌሎች የዲፕሎማሲ ዘርፎች ያላቸውን ተሳትፎ ለመጨመር በትኩረት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል። የተባበሩት መንግስታት አጀንዳ 2030 እንዲሁም ዘላቂ የልማት ግብን ለማሳካት የጾታ እኩልነትን መሰረት ያደረገ ተግባር ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ጨምረዋል። ሴቶች በሰላምና ጸጥታ መከበር ያላቸውን ተሳትፎ ለመጨመር የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት እ.አ.አ በ2000 ያሳለፈው የውሳኔ ሀሳብ ቁጥር 1325 ትግበራ ላይም ውይይት ተደርጓል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግስታት ውሳኔ 1325 ትግበራ በብሔራዊ የድርጊት መርሀ ግብር የሰጠችውን ትኩረትና ሂደት ዘርዝረዋል። በውሳኔው የተቀመጡ ጉዳዮችን ከሀገሪቱ መርሀ ግብሮች ጋር በማጣጣም በሰላምና ጸጥታ፣ በሀገራዊ ምክክር፣ በአቅም ግንባታ፣ በውሳኔ ሰጪነትና ሌሎች የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በ76ኛ ጠቅላላ ጉባኤው መንግስታት ለሴቶች የዲፕሎማሲ ተሳትፎ የበለጠ ትኩረት እንዲሰጡ ግንዛቤ ለመፍጠርና ግፊት ለማድረግ “የሴቶች በዲፕሎማሲ ዓለም አቀፍ ቀን” እ.አ.አ በየዓመቱ ሰኔ 24 እንዲከበር መወሰኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

 

የዛሬው መርሐ ግብር “የሴቶች በዲፕሎማሲ በኢትዮጵያ ጥምረት” የተዘጋጀ ሲሆን አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮችና ሌሎች ተገኝተዋል ሲል የዘገው ኢዜአ ነው።

Please follow and like us: