የፍልሰት ተመላሾችና መልሶ ማቋቋም መረጃ ማደራጀትና ማጋራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት የተለያዩ ተቋማት ስምምነት ተፈራረመ

(አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2/ 2016 ዓ.ም) የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የፍልሰት ተመላሾችና መልሶ ማቋቋም መረጃ ማደራጀት፣ ማጋራት እና የቴክኒክ ድጋፍ መስጠት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመስራት ከተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ መስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ።

የመግባቢያ ስምምነቱ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እና ሚኒስትሮችና የየተቋማቱ የስራ ኃላፊዎች ፈርመዋል። በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንተናገሩት፤ በሀገራችን በህገወጥ ደላሎች ተታለው በርካታ ዜጎች በህገወጥ መንገድ ከሀገር ሲወጡ፣ በድበር ጠባቂዎችና ሌሎች የተደራጁ አካላት እጅ እየወደቁ፤ ለሞት እየተጋለጡ እንደሚገኝ ገልጸዋል። የኢፌዲሪ መንግስት እየተከተለ ባለው ዜጋ ተኮር ፖሊሲው አማካኝነት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በነበረችበት ጊዜ እንኳን መደበኛ ባልሆነ ፍልሰት ወደ ተለያዩ ሀገራት ሄደው ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ስራዎችን በስፋት ሲያከናውን ቆይቷል አንስተዋል፡፡

ከጥቅምት ወር ወዲህ ብቻ ከሳዑዲ ዓረቢያ፣ ከሱዳን፣ ከየመንና ኦማን 105 ሺህ 602 ዜጎች ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል ብለዋል፡፡ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ለመከላከል፣ ተጎጂዎችን ለመደገፍና መልሶ ለማቋቋም እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን በመረጃ የተደገፈና አሰራሩንም ዘመናዊ ለማድረግ በአውሮፓ ህብረት ድጋፍ የተመላሾችና መልሶ ማቋቋም የመረጃ ቋት (data base) የማልማት ስራ በተለያዩ አካላት ትብብር ሲከናወን መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ የሚቋቋመው ዳታ ቤዝ ለተገልጋዮች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት፣ ለተመራማሪዎች፣ ለጥናት አጥኚዎች፣ ለፖሊሲ አውጪዎችና ለመንግስት አስተማማኝ የመረጃ ምንጭ ሆኖ እንደሚያገለግል ገልጸዋል።

የመግባቢያ ስምምነቱ ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት አገልግሎት ላይ የሚቆይ ሲሆን እንደአስፈላጊነቱ ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚችልም ተጠቅሷል። ስምምነቱ የኢንፎርሜሽንና ቴክናሎጂ ሚኒስቴር፣ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር፣ ፍትህ ሚኒስቴር ፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ጤና ሚኒስቴር፣ የኢንፎርሜሽንና መረብ ደህንነት አስተዳደር፣ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎትና የስደተኞችና ተመላሽ አገልግሎት ፈርመዋል። ዕለቱ በተዘጋጀው የስምምነት ሰነድ እና ፕሮቶኮል ዙሪያ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች አስተያየታቸውን ሰጥተውበታል።

 

Please follow and like us: