Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ባህላዊ የግጭት አፈታት ጥበብን በአግባቡ እየተጠቀምን ለትውልድ ማስተላለፍ ይጠበቅብናል – ወ/ሮ ሂክማ ካይረዲን ሚኒስቴር ዴኤታ
ባህላዊ የግጭት አፈታት ጥበብን በአግባቡ እየተጠቀምን ለትውልድ ማስተላለፍ ይጠበቅብናል ሲሉ የሴቶችና ህፃናት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሂክማ ካይረዲን ገልፁ።

ሚኒስቴሩ ከዩኤን ውመን ጋር በመተባበር “ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች በኢትዮጵያ” በሚል ሃሳብ ዙሪያ ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላትን አቅም ለማጎልበት ያለመ ስልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል። በመድረኩ ላይ የተገኙት የሴቶችና ህፃናት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሂክማ ካይረዲን ግጭት በሚከሰትበት ወቅት ሁሉንም ዜጎች በተለይ ደግሞ ሴቶች፣ ህፃናት፣ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞችን ይበልጥ ተጎጂ እንደሚያደርግና በሀገር ላይም ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያደርስ ጠቁመዋል።

በባህላችንም ሆነ በኃይማኖታዊ አስተምርሆዎች ግጭት አላስፈላጊ መሆኑን ገልፀው ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም ለመገንባት በሚደረገው ሀገራዊ ጥረት ውስጥ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አፅዕኖት ሰጥተዋል። ግጭት በተለያዩ ምክንያቶች ሊፈጠር የሚችልና ተፈጥሯዊ ቢሆንም በየአካባቢው ያሉ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎችን በመጠቀም አለመግባባቶችን መፍታትና ትውልድን ማዳን እንደሚገባም አስገንዝበዋል። ሰላምን በማስፈን ረገድ ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ስርዓት ጉልህ ሚና እንዳለው የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ፥ ይሁንና ስርዓቱ በመጤ ልማዶች ሳቢያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረና ጠቃሚ ባህላዊ እሴቶቻችንንም እያሳጣን ይገኛል ብለዋል።

በመሆኑም ለሀገር ሰላምና ግንባታ ከሚኖረው ፋይዳ አንፃር በጎ እሴቱን ለማስቀጠል እንደሀገር የተጀመሩ ጥረቶች ሊጠናከሩ እንደሚገባ ተናግረዋል። ባህላዊ የግጭት አፈታት ጥበብን በአግባቡ እየተጠቀምን ለትውልድ ማስተላለፍ ይጠበቅብናል ሲሉም አክለው ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልፀዋል። ስልጠናው በሀገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎች ላይ ያለውን ግንዛቤና የባለድርሻ አካላትን ሚና ለማሳደግ የበኩሉን እገዛ እንደሚያደርግ ጠቁመው ተሳታፊዎች ያገኙትን እውቀት በስራ ላይ እንዲያውሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በስልጠናው ከትግራይ፣ ከኦሮሚያ፣ ከአፋር፣ ከጋምቤላ፣ ከቤኒሻንጉል እና ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተውጣጡ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሀደ ሲንቄዎች፣ ሴት የሰላም አምሳደሮች፣ የባህል ፍርድ ቤት ዳኞች፣ የሴትና የወጣት አደረጃጀት ተወካዮች እና የሴቶች የልማት ህብረት ተወካዮች ተገኝተዋል። ስልጠናው በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩርና ለሶስት ተከታታይ ቀናት የሚሰጥ መሆኑን ከወጣው መርሃ-ግብር ለማወቅ ተችሏል።
