ካንሰር በጊዜ ከተደረሰበትና ህክምና ከተደረገለት በቀላሉ ሊድን የሚችል በሽታ ነው

“አለምፍሬ ፒንክ ሃውስ ካንሰር ፋውንዴሽን” የበጎ አድራጎት ድርጅት አመታዊ የጡት ካንሰር ወርን ምክንያት በማድረግ ‘ብርታትሽ ብርታቴ’ በሚል መሪ ሃሳብ የእግር ጉዞ አካሂዷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ፥ የካንሰር በሽታ በአለማችን ብሎም በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ መምጣቱን ተናግረዋል። በሀገራችን ከግንዛቤ እጥረትና መዘናጋት ጋር ተያይዞ በተለይ በጡትና የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር እየተጠቁና ለህልፈት እየተዳረጉ ያሉ ሴቶች ቁጥር ቀላል እንዳልሆነ ጠቁመዋል። ካንሰር በጊዜ ከተደረሰበትና ህክምና ከተደረገለት በቀላሉ ሊድን የሚችል በሽታ በመሆኑ ሴቶች በየጊዜው የካንሰር ቅድመ ምርመራ የማድረግ ልምድ ማዳበርና በሽታው ስር ሳይሰድ ህክምና መከታተል ይጠበቅባቸዋል ሲሉም አሳስበዋል።

ሚኒስቴሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ሴቶች ቅድመ ምርመራ ማድረግ እና የህክምና አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እያከናወነ ያለውን የግንዛቤና የንቅናቄ ስራ አጠናክሮ ይቀጥላል፤ ድጋፍም ያደርጋል ብለዋል። የጤና ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር መቅደስ ዳባ በዚሁ ጊዜ፥ ሚኒስቴሩ ካንሰርን ለመከላከልና አክሞ ለማዳን የሚያስችል ስትራቴጂ ነድፎ በርካታ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል። የታመሙትንና እየታከሙ ያሉትን ወገኖች ሁላችንም አለን ልንልና ልንደግፋቸው ይገባል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የ”አለምፍሬ ፒንክ ሃውስ ካንሰር ፋውንዴሽን” የበጎ አድራጎት ድርጅት መስራችና ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፍሬህይወት ደርሶ በበኩላቸው፥ ድርጅቱ ከተለያዩ ክልሎች ለጡትና የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ህክምና ወደ ጥቁር አንበሳ እና ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለሚመጡና ማረፊያ ለተቸገሩ ወገኖች የምግብ፣ የመጠለያና የትራንስፖርት አገልግሎት በነፃ በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

 

Please follow and like us: