Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ህብረ ብሔራዊ የፌዴራል ስርዓት እውን መሆን ለሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት የበኩሉን አስተዋፅዖ ማበርከቱ ተገለፀ
የፌዴሬሽን ምክር ቤትና የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በመተባበር ህብረ ብሔራዊ ፌደራላዊ ስርዓት ግንባታው እየገጠሙት ያሉት ተግዳሮቶች እና የመፍትሔ ሐሳቦች ላይ ያተኮረ የአሰልጣኞች ስልጠና መድረክ ተዘጋጅቷል።

በስልጠናው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ ዘሃራ ዑመድ፥ ህብረ ብሔራዊ ፌደራላዊ ስርዓት የሰላም መገንቢያ፣ የልማት መሰረት፣ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ዋልታና የአንድነትን መገንቢያ መሣሪያ ነው ብለዋል። ህብረ ብሔራዊ የፌዴራል ስርዓት እውን መሆን የሴቶች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎና እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበኩሉን አስተዋፅዖ ማበርከቱን ገልፀዋል። የዘንድሮው 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ቀን “አገራዊ መግባባት ለብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር ጠቁመዋል።

የስልጠናው ዋና ዓላማም እንደየአካባቢው ሁኔታ የተፈጠሩ ተግዳሮቶችን ነቅሶ በማውጣት እና በመመካከር በመፍትሔዎቻቸው ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ ለመያዝና አገራዊ መግባባት ለመፍጠር ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ምክትል አፈጉባኤዋ አስምረውበታል። የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶችና ህጻናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሒክማ ከይረዲን በበኩላቸው አለም አቀፍ የነጭ ሪቫን ቀን መከበር “ለስርዓተ ፆታ እኩልነት የወንዶች ሚና /አጋርነት/” አስፈላጊ መሆኑን የሚያመላክት ወሳኝ ኩነት መሆኑን ገልፀዋል። እንዲሁም “ህጻናት የሚሉት አላቸው እናድምጣቸው” በሚል መሪ ቃል የዘንድሮ ዓለም አቀፍ የህጻናት ቀን እንደሚከበር ገልፀው የህጻናትን ጥያቄ ማድመጥና ተገቢ ምላሽ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

ሀገራዊና ዓለም አቀፍ ኩነቱን ምክንያት በማድረግ በሚካሄዱ ሰፋፊ የንቅናቄ ስራዎች የሴቶችንና ህፃናትን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ መታቀዱን ጠቁመው ለጋራ ዕቅዱ መሳካት ሁሉም የሴቶችና የህፃናት አደረጃጀት መዋቅሮች በትብብርና በቅንጅት እንዲሰሩ ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ መልዕክት አስተላልፈዋል።
