Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ሚኒስቴሩ ጥቃትን አስቀድሞ ለመከላከል ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን አስተማሪ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል ጠንካራ የህግና የአፈፃፀም ስርዓት እንዲኖር በቅንጅት እየሰራ ይገኛል።
የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሴቶችና ህፃናትን በተመለከተ በሚስተዋሉ የህግ ክፍተቶች፣ መሻሻልና አዲስ መውጣት በሚገባቸው የህግ ማዕቀፎችና በአፈጻፀም ረገድ ባሉ ችግሮች ዙሪያ የምክክር መድረክ በመካሄድ ላይ ነው፡፡

በመድረኩ ላይ የሴቶችና ህፃናት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሒክማ ከይረዲን እንደተናገሩት፤ ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃት በሴቶችና ህፃናት ላይ አካላዊ፣ አእምሯዊና ስነልቦናዊ ጉዳት የሚያደርስና የከፋ የጤና እክልም የሚያስከትል መሆኑን ገልፀዋል። በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች የወንጀል ድንጋጌዎች የተቀመጠላቸው ቢሆንም ከህግ ክፍተቶች በተጨማሪ በትግበራ ወቅት የሚያጋጥሙ የአፈፃፀም ጉድለቶች መኖራቸው በጥናት መለየቱን ተናግረዋል። ችግሩ ጊዜ የሚሰጠው አለመሆኑን አጽንኦት በመስጠት ሚኒስቴሩ ጥቃትን አስቀድሞ ለመከላከል ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን ከደረሰ በኋላ አስተማሪ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል ጠንካራ የህግና የአፈፃፀም ስርዓት እንዲኖር በቅንጅት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

አመለካከቱንም ሆነ ድርጊቱን አጥብቆ ከማውገዝ ባሻገር ጥቃትን ለማስቆም የሚደረገው ሀገራዊ ጥረት እንዲሰምር ሁሉም በጋራ መረባረብ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ስራ አስፈፃሚ ዳይሬክተር ወ/ሪት ሌንሳ በየነ በበኩላቸው ህጉን ማሻሻል ያስፈለገበት ዋነኛ አላማ በሀገራችን እየተጠቀምንበት ያለው የተሻሻለው የቤተሰብ ህግና የወንጀል መቅጫ ህጉ በወቅቱ የነበሩ ነባራዊ ሁኔታዎች ላይ ብቻ ያተኮረ በመሆኑ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ጥናቱ ከፍትህ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ የህግ ሴት ባለሙያ ማህበር እና ከዩኤን ውመን (UNWOMEN) ጋር በመተባበር መካሄዱንና በተለያዩ ጊዜያትም ምክክሮች ሲደረጉ መቆየቱ ተመላክቷል።
በጀስቲስ ሺልድ እና በተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ቢሮ በኩልም ተጨማሪ ግብዓት መሠጠቱም ተጠቁሟል። በዚህ መድረም የህግ ክፍተትና የአፈፃፀም ችግሮች እንዲሁም የወሲባዊ ጥቃት አድራሾች የምዝገባ ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ የተዘጋጁ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጓል። በቀጣይ ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች፣ የህጻናትና የአካል ጉዳተኞች የተጠቃለለ ህግ ማዘጋጀት አስፈላጊነት ላይ ውይይቱ እንደሚቀጥል ተገልጿል።
