Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ባለፉት ስድስት ወራት ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑትን ዜጎች ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ
የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮጀክት የ6 ወር ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ተገመግሟል።

በመድረክ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማህበራዊ ጥበቃ፣ ማስተባበሪያና መከታተያ መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ተስፋዬ ሽፈራው ተገኝተው እንደገለፁት፤ መንግስት ኑሯቸውን በከተሞች ያደረጉና በማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲው ደሀና ተጋላጭ ተብለው የተለዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከድህነት ወጥተው ራሳቸውን ከመቻል ባሻገር በአገር ግንባታ ሒደት ውስጥ የሚኖራቸውን አስተዋፅኦ ከፍ ለማድረግ ከ2008 ዓ,ም ጀምሮ የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮጀክት ተግባራዊ ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰዋል። ባለፉት ስድስት ወራትም ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑትን ወገኖች ህይወት ለማሻሻልና ለመለወጥ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸው ገልፀዋል።

ስራ አስፈፃሚው እንዳሉት፣ በገንዘብ ድጋፍና በመሰረታዊ የማህበራዊ አገልግሎቶች ትስስር መፍጠር ረገድ መጠነ ሰፊ ተግባራት መከናወናቸውንና በዚህም በርካታ ወገኖችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል። በቀጣይም በከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮጀክት ለዜጎች የሚሰጡ የማህበራዊ አገልግሎቶች የተጠቃሚዎችን መብት፣ ደህንነትና ክብር የሚያስጠብቁና ለጉዳትም የማያጋልጡ ሊሆኑ የሚያስችሉ አሰራሮች መዘርጋትና ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ለዚህም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለፕሮግራሙ ውጤታማነትና ለዜጎች የተሻለ ተጠቃሚነት የማስተባበር፣ የመምራትና የመደገፍ ሃላፊነቱን ይወጣል ብለዋል።
በመድረኩ የቋሚና ጊዜያዊ ድጋፍ ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት የተደረገ ሲሆን መድረኩ ተሞክሮዎች ተለይተው እንዲሰፉ፣ የተስተዋሉ የአሰራር ክፍተቶች እንዲታረሙ፣ በቀጣይ ለዜጎችን የተሻለ አገልግሎት የሚያስችል አሰራር ለማጎልበትና አፈፃፀሙን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተገልጿል።
በእቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረኩ ላይ የፌደራል፣ የክልልና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች አመራሮች እና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛል።
