Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የመረጃ ነፃነት፣ መረጃ የማግኘት መብት እና መረጃን ተደራሽ የማድረግ ግዴታ

የመረጃ ነፃነት፣ መረጃ የማግኘት መብት እና መረጃን ተደራሽ የማድረግ ግዴታ
መግቢያ
ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ዓለም አቀፋዊ መብት ሲሆን ኢትዮጵያ ተቀብላ ባጸደቀችው የሰብዓዊ መብቶች ሁሉን አቀፍ መግለጫ (UDHR፣1948) አንቀፅ 19 ላይ እንደተቀመጠው ማንኛውም ሰው ሀሳቡን በነፃነት የመግለጽና የመሰለውን አስተያየት የመስጠት መብት አለው። ይህ መብት ያለምንም ተፅዕኖ እና ጣልቃ ገብነት በማናቸውም ዓይነት መገናኛ መረጃዎችና ሀሳቦችን የመፈለግ፣ የመቀበልና የማስተላለፍ ነፃነትን እንደሚጨምር በድንጋጌው ላይ ሰፍሮ ይገኛል።
በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 29 (4) ላይ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች ሀሳቦችና አመለካከቶች በነፃ መንሸራሸራቸውን ለማረጋገጥ ሲባል የመገናኛ ብዙኃን በተቋምነታቸው የአሰራር ነፃነትና የተለያዩ አስተያየቶች የማስተናገድ ችሎታ እንዲኖራቸው የሕግ ጥበቃ ይደረግላቸዋል።
የመገናኛ ብዙኃን መሰረታዊ ተግባር መረጃን ከአንድ ወገን ወደ ሌላው ማሰራጨት እንደመሆኑ መጠን ይህን መረጃ የማሰራጨት ተግባራቸውን በአግባቡ መወጣት እንዲችሉ መረጃዎቹን በነፃነት ማግኘት መብት አላቸው። በዚህ አጭር የንቃተ ሕግ ጽሁፍ ስለ መረጃ ነፃነት፣ መረጃ የማግኘት መብትና መረጃን ለሚዲያዎች ተደራሽ ከማድረግ አኳያ ስለሚኖር ግዴታና ግዴታውን አለመወጣት የሚያስከትለውን ተጠያቂነት ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡
የመረጃ ነፃነት ምንነት
የመረጃ ነፃነት የሚለውን ሐረግ ምንነት ከማየታችን በፊት መረጃ የተባለው ወሳኝ ቃል ምንድን ነው የሚለውን ማየቱ ጠቃሚ ይሆናል። የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 አንቀፅ 2(6) ላይ “መረጃ ማለት በማንኛውም ዓይነት ቅርፅ የተቀናበረ ማንኛውም ዓይነት ሰነድ ነው” ሲል ትርጉም ሰጥቶታል። በዚህም መሰረት መረጃ ማንኛውም ቅጂ፣ ምልልስ፣ ጥሬ ሀቅ፣ የግል አስተያየት፣ ምክር፣ የውስጥ ማስታወሻ፣ ዳታ፣ ስታቲስቲክስ፣ መፅሐፍ፣ ሥዕል፣ ዕቅድ፣ ካርታ፣ ዲያግራም፣ ፎቶግራፍ፣ የድምፅ ወይም የምስል ቅጅ፣ ወይም ማንኛውም ሊጨበጥ የሚችልና የማይጨበጥ ቁስ ሊያጠቃልል ይችላል (አማኑኤል አብርሀም “የመረጃ ነፃነት በኢትዮጵያ” ከተሰኘው መፅሐፍ)።
የመረጃ ነፃነት ሲባል ደግሞ የሰዎች የመናገር ወይም ሀሳብን የመግለፅ፣ መረጃ የመፈለግ፣ የማግኘትና የማስተላለፍ መብትን ያካተተ ሰፊ ፅንሰ ሀሳብ ነው። የመረጃ ነፃነት መኖር ዜጎች የሀገራቸውን ጉዳይ እንዲረዱና በተገቢው ሁኔታ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ከማስቻሉም በላይ፤ መብትና ግዴታቸውን ተረድተው ስለመብታቸው እንዲጠይቁና ሀገራዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ ያስችላቸዋል።
መረጃ የማግኘት መብት
መረጃ የማግኘት መብትን በሕገ-መንግስት አንቀፅ 29(2) እንደተመለከተው ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሀሳቡን የመግለፅ ነፃነት ያለው ሲሆን ይህ ነፃነት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በፅሁፍ ወይም በህትመት፣ በሥነ ጥበብ መልክ ወይም በመረጠው ማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ፣ ማንኛውንም አይነት መረጃና ሀሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨት ነፃነትን የሚያካትት እንደሆነ በግልፅ ተቀምጦ እናገኘዋለን (አዋጅ ቁጥር 1238/13 አንቀፅ 48ን ይመለከታል)።
ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት በኢትዮጵያ ሕገ-መንግስት መሰረት ዴሞክራሲያዊ መብት በመሆኑ ይህ መብት ሊገደብ የሚችልበት ሁኔታ አለ። በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 29(6) እንደተመለከተው የወጣቶችን ደህንነት፣ የሰውን ክብርና መልካም ስም ለመጠበቅ ሲባል ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ላይ ሕግን መሰረት ያደረገ ገደብ ሊደረግ ይችላል። ሌላው ጦርነትን የሚቀሰቅሱ እንዲሁም ሰብዓዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ መግለጫዎች ከላይ በተጠቀሰው አንቀፅ መሰረት በሕግ የተከለከሉ እንደሆነ ተመላክቷል።
ዜጎች ወይም ማንኛውም ህጋዊ የሚዲያ አካል መረጃን በተቻለ መጠን በፍጥነትና በዝቅተኛ ወጭ የማግኘት መብት አላቸው። የመረጃ ጥያቄ በፍጥነትና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መስተናገድ አለበት። ይህን ሊፈታ የሚችል የመረጃ ጥያቄ አቀረራብና ቅሬታ አሰማም ሥርዓት ያስፈልገዋል። መረጃን የማግኘት መብት በመረጃ ፈላጊው አካል ሲጠይቅ እና ሳይጠየቅ የሚፈፀም መብት ሲሆን መረጃ ሳይጠየቅ መረጃ የማግኘት መብት የሚተገበረው መረጃው በመንግስት አካል ሲገለፅ ነው። የመንግስት አሰራር ለሕዝብ ግልፅ በሆነ መንገድ እና በተጠያቂነት መርህ መከናወን እንዳለበት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 12 ላይ ተደንግጎ ይገኛል። የመንግስት አካላት በግልፅነትና በተጠያቂነት መንፈስ ስራቸውን ማከናወን ያለባቸው በመሆኑ ለህዝብ መገለፅ ያለባቸውን ጉዳዮች በተለያዩ መረጃ ማሰራጫ መንገዶች የማሳወቅ ግዴታ አለባቸው።
በጠቅላላው መረጃን የማግኘት መብትን በአዋጅ ቁጥር 590/2000 አንቀፅ 12 ላይ እንደሚከተለው ተደንግጓል፡-
ማንኛውም ሰው ከማንኛውም መንግስታዊ አካል መረጃን የመጠየቅ፣ የማግኘትና የማስተላለፍ መብት አለው፤
በመንግስት ተቋም የሚገኝን መረጃ የመመልከት፣ ማስታወሻ የመያዝና ግልባጭ የመውሰድ መብት አለው።
መረጃን ለሚድያ ተደራሽ የማድረግ ግዴታ
መገናኛ ብዙሃን የሚያሰራጩት መረጃ የመንግስትን የአሰራር ግልፅነት፤ ተጠያቂነትና ውጤታማነት በመመዘን የመንግስት አሰራርንና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከመቅረፍ አኳያ ከፍተኛ ሚና አላቸው። በመሆኑም የመንግስት አካላት መረጃን ለመገናኛ ብዙኃን ተደራሽ የማድረግ ግዴታ አለባቸው። በመረጃ ነፃነት ሕጉ መረጃ የማግኘት መብትና መረጃን የመስጠት ግዴታን አስመልክቶ የሚከተሉትን ዓላማዎች ለማሳካት ሊተገበሩ እንደሚገባቸው በአንቀፅ 10 ስር ደንግጓል። እነዚህም፡- ሕግን መሰረት ያደረጉ ገደቦች እንደተጠበቁ ሆነው ማንኛውም መንግስታዊ አካል ዜጎች መረጃን ለመጠየቅ፣ ለማግኘትና ለማስተላለፍ ያላቸውን መብት ተፈፃሚ የማድረግ፤ መረጃ ፈላጊዎች መረጃዎችን በተቻለ ፍጥነትና በዝቅተኛ ወጪ ሳይደክሙ የሚያገኙበትን አሰራርና ስነ-ስርዓት በመመስረት መብቱን ተፈፃሚ የማድረግ እና የሕዝብ ተሳትፎን የስልጣን ባለቤትነትን የማረጋገጥና እንዲሁም የአሰራር ግልፅነት፣ ተጠያቂነትና ውጤታማነት የሰፈነበት የመንግስት አሰራርንና መልካም አስተዳደርን የማጠናከር ዓላማን መሰረት አድርጎ የሚተገበር ይሆናል።
መረጃን ለሚድያ ተደራሽ አለማድረግ የሚያስከትለው ተጠያቂነት
መረጃን ተደራሽ የማድረግ ጉዳይ በግዴታነት መቀመጡ ብቻ በቂ አይሆንም። ግዴታው በአግባቡ ተግባር ላይ እንዲውልና እንዲፈፀም አስገዳጅ ሕግ ሊቀመጥለት ይገባል። ሰዎች በሕግ የተጣለባቸውን ግዴታ እንዲወጡ ከሚያስችሉት መንገዶች ዋነኛው ሕጉን በሚጥሱት ላይ ተመጣጣኝ ቅጣት መጣል ነው። በያዝነው ርዕሰ ጉዳይ ላይም የመረጃ ነፃነት አዋጁ መረጃን ተደራሽ የማድረግ ግዴታቸውን በማይወጡት ላይ የሚከተለውን ቅጣት አስቀምጧል። በዚህም መሰረት ማንም ሰው መረጃ የማግኘት መብትን ለመጣስ በማሰብ ማንኛውንም ሰነድ ያጠፋ፣ ያበላሸ፣ የቀየረ፣ የሰረዘ፣ የደበቀ፣ በተንኮል የከለከለ፣ ያፋለሰ ወይም ሀሰተኛ ሰነድ የሰራ በገንዘብ መቀጮ ወይም ከሁለት ዓመት በማይበልጥ እስራት እንደሚቀጣ ተደንግጓል (አንቀፅ 39(5))።
ማጠቃለያ
በጠቅላላው ማንኛውም ሰው በተለይም የመገናኛ ብዙኃን ከማንኛውም አካል በዋናነት ከመንግስት አካላት መረጃን የማግኘት እና የማሰራጨት ሕገ-መንግስታዊ መብታቸው መሆኑንና የመንግስት አካላትም መረጃዎችን ለሕዝብ በተለይም ለመገናኛ ብዙኃን በፍጥነት፣ በዝቅተኛ ወጪ ተደራሽ የማድረግ ግዴታ ያለባቸው መሆኑ በመረጃ ነፃነት አዋጁ ሰፍሯል። አዋጁ በዚህ ብቻ ሳይወሰን ሕጉን በሚተላለፉት ላይ ተመጣጣኝ ቅጣት የጣለ ስለሆነ የመንግስት አካላት ይህንን ተገንዝበው በሕግ እገዳ ከተጣለባቸው መረጃዎች ውጪ ያሉትን በሙሉ ለመገናኛ ብዙኃንና ለሕዝብ በተገቢው መንገድ ተደራሽ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
በመላኩ ባዩ
