በጎ ማሰብና ማድረግ ከክብርም ከሰውነትም በላይ ነው!!

የበጎ አድራጎት ተግባራት ሰዎች ውስጣቸው ከሚሰማቸው የሰብዓዊነት ስሜት በመነጨ ለሚኖሩበት ማህበረሰብ ለውጥና ለሀገር ልማትና እድገት ይበጃል ያሉትን ያለማንም ቀስቃሽና ጉትጎታ በራሳቸው ተነሳስተው በጎ አመለካከታቸውን፣ ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ እውቀታቸውንና አለፍ ሲልም ሀብታቸውን እሴት በሚጨምሩ ተግባራት ላይ የሚያውሉበት ትልቅ እሴት ነው።

በጎነት ለራስ ነው፤ በጎ ማሰብና ማድረግም እንዲሁ፡፡ በጎነት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው እንደ ስሙ ከበጎ ልቦና፣ ከቅን ህሊና፣ ከንጹህ ፍቅርና ፍጹም ከሆነ መልካምነት የመነጨና በነጻ የሚሰጥ አገልግሎት ሲሆን በምላሹም ጥልቅ ደስታና እርካታን የሚያጎናጽፍ ሰናይ ምግባር ነው፡፡

በጎነትን ማሰብም ሆነ የበጎነት ባህሪን መላበስና በበጎነት ስሜት ህዝባና ሀገርን ማገልገል ትልቅ ክብር ነው፡፡ በራስ ፈቃድ ተነሳስቶ ያውም በነጻ መልካምና በጎ ስራ መስራትና ወገንና ሀገርን ማገልገል መቻል ደግሞ ከክብርም በላይ ነው፡፡

የፈረሰውን ማደስ፣ የተራበውን ከማጉረስ አልፎ ማብላት፣ የበረደውን ማልበስ፣ ያዘነውን ማጽናናት፣ የፈሰሰን እንባ ማበስ፣ የወደቀውን ማንሳት፣ የጠፋውን ሳቅና ደስታ መመለስ፣ ህይወት ማዳንና መታደግ ባጠቃላይም ለወገንና ለሀገር አለሁኝ ማለት – በቅን ልቦና መተባባር፣ መደጋገፍና መረዳዳት ከክብርም ከሰውነትም በላይ ነው።

ወዶና ፈቅዶ ወገንንና ሀገርን መርዳትን የመሰለ አስደሳች ስራና ተግባር የለም ያሉ በርካቶች እንዲህ ዓይነቱን መልካም ስራ ሰርተውና አድርገውት በተግባር ጭምር አሳይተውናል፡፡

ለሜቄዶኒያ አረጋውያን የአእምሮ ህሙማን መርጃ ከየካቲት 1 ቀን ጀምሮ እየተካሄደ ባለው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐግብር ልበ ቅን ዜጎች ያሳዩት ተነሳሽነትና ርብርብ ለዚህ ትልቅ ማሳያ ነው።

ታዲያ ሀሳብ ከማፍለቅ ጀምሮ እነዚህ ልበ ቅን – በጎ አድራጊ ግለሰቦች እና ተቋማት ምንም እንኳን ላበረከቱት አስተዋጽኦ የሚመጥን ባይሆንም ተገቢው ክብርና እውቅና መስጠት ይገባል።

እናም ያለስስት ውድ ጊዜያችሁን፣ ጉልበታችሁን፣ እውቀታችሁንና ገንዘባችሁን ጭምር ለበጎነት ስታበረክቱ የነበራችሁ፣ አሁንም በየዘርፉ የድርሻችሁን እየተወጣችሁ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ – ኢትዮጵያውያን ሀገራችሁ ኢትዮጵያ ታመሰግናችኋለች፤ ታከብራችኋለች፡፡

የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በተጠቃሚ አረጋውያን ወገኖች ስም ከፍ ያለ ምስጋና እያቀረበ፤ ሜቄዶኒያ የሰነቀው ርዕይው እውን ይሆን ዘንድ ሁሉም ከጎኑ እንዲቆምና አቅም የፈቀደውን ሁሉ በማድረግ የዜግነት ድርሻውን እንዲወጣ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባለድርሻና አጋር አካላትን በማስተባበር በተለያዩ ጊዜያት ሜቄዶኒያን ጨምሮ ልዩ ድጋፍና ክብካቤ ለሚሹ ወገኖች አገልግሎት እየሰጡ ለሚገኙ ሌሎች የበጎ አድራጎት ተቋማት ሲያደርግ የቆየውን የዓይነት፣ የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ ወደፊትም የበለጠ አጠናክሮ የሚቀጥልና ማህበራዊ ሃላፊነቱንም የሚወጣ ይሆናል።

Please follow and like us: