ከፍተኛ የውሣኔ ሰጪነት ቦታ በሌሎች ቸርነት የሚሰጥ ሳይሆን በጽኑ ፍላጎት፣ ተነሳሽነትና ራስን ለማብቃት በሚደረግ ጥረት የሚገኝ ነው – ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)

ከፍተኛ የውሣኔ ሰጪነት ቦታ በሌሎች ቸርነት የሚሰጥ ሳይሆን በጽኑ ፍላጎት፣ ተነሳሽነትና ራስን ለማብቃት በሚደረግ ጥረት የሚገኝ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚንስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ገለፁ።

ይህ የተገለፀው የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ የሴቶች የአመራርነትና ውሳኔ ሰጪነት የአቅም ግንባታ ስልጠና ሰልጣኞችን ባስመረቀበት ወቅት ነው። በምርቃት ስነስርዓቱ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚንስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንደገለፁት፣ መንግስት ሴቶች ያሉባቸውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች በመፍታት ለአገራችን እድገት፣ ልማትና ለውጥ ግንባር ቀደም ተዋናይ እንዲሆኑ እየሠራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

ለዚህም ሴቶች በሁሉም መስክ ያላቸው ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ለማስቻል የሚያግዙ ልዩ ልዩ የህግ ማዕቀፎችንና ስትራቴጂዎችን ቀርጾ በሥራ ላይ ከማዋሉም በላይ ለስኬታማ ትግበራቸውም ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በተለይ በአመራርነትና ውሳኔ ሰጪነት ላይ ያተኮረ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና በመስጠት የሴት አመራሮችን ቁጥር ከፍ ለማድረግና ሴቶችን ለማብቃት በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል። በተጨማሪም የሴት አመራር ቋት በማዘጋጀትና በየደረጃው ለሚመለከታቸው የመንግስት መዋቅሮችና የስራ ኃላፊዎች በማሳወቅ ለተግባራዊነቱ ጥብቅ ክትትል እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ዛዲግ አብረሃ በበኩላቸው አካዳሚው ለሴቶች አመራር ሰጪነት ስልጠና ፕሮግራም ልዩ ትኩረት በመስጠት እየሠራ እንዳለ ገልፀው የሴቶች ችግር በፍጥነት ካልተፈታ ቤተሰብን፣ ግለሰቦች፣ ወንዶችን ሀገርን ለማበልፀግና ትውልድን ለማፅናት የምንጥረው ጥረት ከንቱ ልፋት ሆኖ ይቀራል ብለዋል።

ለዚህም አካዳሚው የመጀመሪያ በሆነው የሴቶች የአመራር ልማት መርሃ-ግብር ያበቃቸውን ሴት አመራሮች ካለው አቅም በተጨማሪ ከተባባሪና አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት ሴቶችን በአመራር ብቁ ሊያደርጉ የሚችሉ የተለያዩ አጫጭር የስልጠና መርሀ ግብሮችን በማዘጋጀት ዛሬ 50 መካከለኛ አመራር ሰልጣኞችን ለማስመረቅ መብቃቱን ገልፀዋል።

Please follow and like us: