እንደሀገር ዘላቂና አስተማማኝ የማህበራዊ አገልግሎት ተጠቃሚዎች መረጃ የምዝገባ ስርዓት ለመዘርጋት ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለፀ

ሀገራዊ የማህበራዊ አገልግሎት ተጠቃሚዎች መረጃ የምዝገባ ስርዓት የሚገኝበት ደረጃና የተቋማት ሚና ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከህንዱ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እና ከብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ጋር በመተባበር የማህበራዊ አገልግሎት ተጠቃሚዎች መረጃ ምዝገባ የዲጂታል ስርዓት ለማልማት በትኩረት እየተሰራ ይገኛል። የዲጂታል ስርዓቱ የማህበራዊ አገልግሎት ተጠቃሚዎችን መረጃ በትክክል ለመመዝገብና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንደሚያስችል የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ ገልፀዋል። ስርዓቱ ለማህበራዊ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ማዕከላዊ የመረጃ ቋት ሆኖ የተጠቃሚዎችን መረጃ በትክክል የሚመዘግብ እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ውጤታማ የማህበራዊ ጥበቃ ስርዓቶችን ለመዘርጋት ያስችላል ብለዋል።

የማህበራዊ አገልግሎት ተጠቃሚዎች መመዝገቢያ ስርዓት እንደ ሀገር ወጥና ትክክለኛ መረጃ እንዲኖር፣ ድግግሞሽን በማስቀረት እኩል የሃብት ክፍፍል እንዲኖር፣ ተጠያቂነትን ለማስፈን፣ የማህበራዊ ጥበቃ ፕሮግራሞችን አፈፃፀም እና ተፅእኖ ለመገምገም፣ የማሻሻያ ቦታዎችን በመለየት እና የአገልግሎቶችን ቀጣይነት ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑንም አያይዘው ተናግረዋል። መረጃ ሃብት መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ የተደራጀና አሁናዊ (real-time) መረጃ መያዝ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥና በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ለመስጠት አይነተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

በመሆኑም እንደሀገር ዘላቂና አስተማማኝ የዲጂታል ስርዓቱ ለመዘርጋት ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ገልፀዋል። የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሰመረታ ሰዋሰው በኩላቸው የዲጂታል ስርዓቱ ለዜጎችም ለሀገርም የሚኖረው ፋይዳ የላቀ በመሆኑ ለስኬታማነቱ በጋራ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

Please follow and like us: