Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የዲጂታል ከባቢው አካታች፣ ለህጻናት ምቹና ከደህንነት ስጋት ነፃ እንዲሆን ጠንካራ አሰራር መዘርጋት እንደሚገባ ተገለፀ
አለም አቀፉ ደህንቱ የተጠበቀ የበይነ-መረብ/ኢንተርኔት አጠቃቀም ቀን “ደህንነቱ የተጠበቀ የበይነ መረብ አጠቃቀምን ለታዳጊ ሕጻናት በማስተማር ትውልድን እናስቀጥል!” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ መርሐግብሮች ተከብሯል።

በመድረኩ የተለያዩ የጥናት ውጤቶች ቀርበው ግንዛቤ እንዲያዝበት የተደረገ ሲሆን በችግሩና መፍትሔው ዙሪያ ለመሞከር ያለመ የፓናል ውይይትም ተካሂዷል።የሴቶችናህፃናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሂክማ ከይረዲን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በህጻናት ላይ በበይነ መረብ በታገዘ መልኩ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወነ ይገኛል፡፡የህጻናትን የኢንተርኔት አጠቃቀም ክህሎት ማዳበርና ደህንነቱ የተጠበቀ የአጠቃቀም ስርዓት ልምድን እንዲያዳብሩ መስራት፣ መልካም አጋጣሚዎችንና ያለውንም ተጽእኖ መረዳት እንዲችሉ ማብቃት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረዋል።በተለይም ወላጆች የልጆቻቸውን የኢንተርኔት አጠቃቀም በተቻለ መጠን መከታተል፣ በገጠመኞቻቸው ዙሪያ ግልጽ ውይይትና መግባባት መፍጠር፣ በተቻለ መጠንም የአጠቃቀም ደንብ እንዲኖር ማስቻል ይገባል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ፈጣን የቴክኖሎጂ እድገት እና የኢንተርኔት ተደራሽነት እየታየ በመምጣቱ የዲጂታል ከባቢው አካታች፣ ለህጻናት ምቹና ከደህንነት ስጋት ነፃ እንዲሆን ጠንካራ የአሰራር ስርዓት መዘርጋት ይገባል ብለዋል። የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ በበይነ መረብ በታገዘ መልኩ በህጻናት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት ሁሉም አካል የበኩሉን ሃላፊነት እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።የዩኒሲፍ የህፃናት ጥበቃ ሀላፊ ጆላንዳ ቫን በበኩላቸው፤ ህፃናት በብይነመረብ ለፃታዊ ጥቃት እየተጋለጡ በመሆኑ ታዳጊ ህፃናትን ከኢንተርኔት ጥቃት ለመጠበቅ በጋራ መሰራት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

የህፃናት መብትና ደህንነት መሪ ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ዘቢደር ቦጋለ በበኩላቸው፥ ደህንነቱ የተጠበቀ የበይነ መረብ አጠቃቀም እንዲኖር ለማስቻል የስልጠና ማኑዋል በቅንጅት መዘጋጀቱን ገልፀዋል። በቀጣይም በየደረጃው የማህበረሰቡን፣ የቤተሰብንና የህፃናትን እውቀትና ክህሎት ለማሳደግ በትኩረት ይሰራል ብለዋል። በተመሳሳይ በህፃናት ላይ ጥቃቶች ሲደርሱ የሪፖርትና የጥቆማ ስርዓት እንዲኖር እንዲሁም ተገቢውን የፍትህ ምላሽ እንዲያገኙ የፖሊስ፣ የህግና የማህበራዊ ሰራተኞችን ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዓሉ ላይ ከፍትህ፣ ከፖሊስ፣ ከኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ፣ ከመረጃ መረብ ደህንነት እስተዳደር፣ ከኢትዮቴሌኮም፣ ከጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ከህጻናት ፓርላማ ተወካዮች እና ሌሎች መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የተውጣጡ አካላት ተገኝተዋል።
