በንግድ መስክ የተሰማሩ ሴቶችን ለማብቃትና የዲጂታል ኢኮኖሚ ስርዓቱ ተጠቃሚ ለማድረግ በቁርጠኛነት መስራት ይገባል

በንግድ መስክ የተሰማሩ ሴቶችን ለማብቃትና የዲጂታል ኢኮኖሚ ስርዓቱ ተጠቃሚ ለማድረግ በቁርጠኛነት መስራት እንደሚገባ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገለፁ።

በካናዳ ኤምባሲ ትብብር የተዘጋጀውና የኢትዮ – ካናዳ ሴቶች ንግድ ላይ ያተኮረ የፖናል ውይይት በስካይላይት ሆቴል ተካሂዷል፡፡ የፖናል ውይይቱ በዋነኝነት በኢትዮጵያና በካናዳ በተለያዩ የንግድ ስራዎች የተሰማሩ ሴቶች በዘርፉ ያላቸውን ልምድና ተሞክሮ እንዲለዋወጡና የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውንም እንዲያጠናክሩ ለማስቻል ያለመ መሆኑን ተመልክቷል። በመድረኩ ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በኢትዮጵያ በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ የተሰማሩ ሴቶች ሰፊውን የንግድ ዘርፍ እንደሚሸፍኑና ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው ገልፀዋል።

በንግድ ስራ የተሰማሩ ሴቶች የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ህይወት ከመለወጥ ባሻገር ለማህበረሰብና ለዘላቂ ዕድገት ጉልህ አስተዋፅዖ ያበረክታሉ ብለዋል። ሆኖም ከዘርፉ የሚገባቸውን ያህል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከገበያ መረጃና ትስስር፣ ከፋይናንስ አቅርቦት፣ ከንግድ ፈጠራ ክህሎት ጋር በተያያዘ ያሉባቸውን ተግዳሮቶች መፍታት ይገባል ሲሉም ተናግረዋል። በንግድ መስክ የተሰማሩ ሴቶችን ለማብቃትና የዲጂታል የኢኮኖሚ ስርዓቱ ተጠቃሚ ለማድረግ በቁርጠኛነት መሰራት እንደሚገባ ክብርት ሚኒስትሯ ገልፀዋል።

በቀጣይ በዘርፉ ሴቶችን ለማብቃት፣ ችግሮቻቸውን ለመፍታትና የኢኮኖሚ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ባለድርሻ አካላት በትብብር እንዲሰሩም ጠይቀዋል። በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር ጆሽዋ ተባህ በበኩላቸው፥ ሴቶች በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና በንግዱ ዘርፍ የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አጋርነትን ማጠናከር፣ ማብቃትና መደገፍ ያስፈልጋል ብለዋል። ለዚህም ካናዳ ሴቶች በዘርፉ ውጤታማ እንዲሆኑ በትብብር እንደምትሰራና ድጋፍም እንደምታደርግ ተናግረዋል።

 

Please follow and like us: