የዜጎችን እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የድጋፍ ስርዓታችንን እናሻሽል!

አለም አቀፍ ዳውን ሲንድረም ቀን በተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ እ.ኤ.አ ማርች 21 / ከ2013 ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት በየዓመቱ መከበር የጀመረ ሲሆን ዘንድሮ በዓለም ለ14ኛ ጊዜ በሃገራችን ደግሞ ለ10ኛ ጊዜ “የድጋፍ ስርዓታችንን እናሻሽል!” /Improve our support system/ በሚል መሪ ቃል በተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐግብሮች በመከበር ላይ ይገኛል፡፡ የአእምሮ እድገት ውሱንነት (Down Sybndrome) ማለት – የአእምሮ ብስለት ጉልህ በሆነ ልዩነት ከአማካዩ በታች መሆንና የግላዊና ማህበራዊ ክንዋኔዎች ብቃት መጓደል ማለት ነው። የአእምሮ እድገት ውሱንነት ያለባቸው ህጻናትና ወጣቶች በአእምሮአዋ እድገታቸው በስሜት ህዋሳታቸው መዳበርና በማህበራዊ ግንኙነቶች ከእድሜ እኩዮቻቸው አንጻር ውሱንነት የሚታይባቸው ናቸው፡፡

በመላው ዓለም የሚገኙ ዳውን ሲንድረም ያለባቸው ወገኖች፣ ቤተሰቦቻቸውና በአጋር አካላት ጥምረት የሚከበረው ዓለም አቀፉ የዳውን ሲንድረም ቀን በሃገራችን በ”ፍቅር ኢትዮጵያ የአእምሮ እድገት ውሱንነት ብሔራዊ ማህበር” አስተባባሪነት እየተከበረ ይገኛል። የበዓሉ ዋና ዓላማ ዳውን ሲንድረም ያለባቸው ዜጎች መብቶች ለማስከበር፣ በሁሉም ዘርፎች አካታችነትን ለማረጋገጥና ሰብዓዊ ደህንነታቸውን ለማስጠበቅ ይቻል ዘንድ የድጋፍ ስርዓትን ለማሻሻል የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ድምጻቸውን በጋራ ለማሰማት ነው፡፡

በዚህ ሃገር አቀፍ የንቅናቄ መርሐግብር ዳውን ሲንድረም ያለባቸው ዜጎች አርኪና ትርጉም ያለው ህይወት እንዲመሩ ለማድረግ፣ አካታች የድጋፍ ስርዓቶችን እንዲጠናከርና የድጋፍ ስርዓቱን በዘላቂነት ለማሻሻል ለመደገፍ የሚያስችል የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት አዎንታዊ ለውጥ ለማምጣት ከፍተኛ ጥረት የሚደረግ ይሆናል። ዳውን ሲንድረም ያለባቸውን ልጆች ዘላቂ ተጠቃሚ ለማድረግ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራው ዲቮራ ፋውንዴሽን “የመጋቢትን ወር ከዲቮራ ጋር!” በሚል በመስቀል አደባባይ የተዘጋጀው ታላቅ ሃገር አቀፍ የንቅናቄ መድረክ የዚህ መርሃ ግብር አንድ አካል ነው፡፡

Please follow and like us: