በተመድ ዋና ፅ/ቤት በአሜሪካን ኒው ዮርክ ሲካሄድ የቆየው 69ኛው አለም አቀፍ የሴቶች ጉባኤ (CSW) ተጠናቀቀ

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፅ/ቤት፣ በአሜሪካን ኒውዮርክ ሲካሄድ የቆየው 69ኛው አለም አቀፍ የሴቶች ጉባኤ (Commission on the Status of Women) የቀጣይ 5 ዓመት የቤጂንግ መግለጫ አፈፃፀምን ለማፋጠን የሚረዳ የማስፈፃሚ የድርጊት መርሐግብር በማፅደቅ ተጠናቅቋል።

ጉባኤው በዋነኝነት የቤጂንግ መግለጫና የድርጊት መርሐግብር ፀድቆ በስራ ላይ የዋለበት 30ኛ አመትን በማስመልከት የድርጊት መርሐግብሩን አፈፃፀም በመገምገም ላይ ያተኮረ ነበር። ኢትዮጵያም በልኡካን ቡድኖች በመወከል ከተለያዩ መንግስታትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት የጎንዮሽ መድረኮች ያዘጋጀች ሲሆን ከተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ጋር በሴቶችና አረንጓዴ ኢኮኖሚ ላይ የተካሄደው ለአብነት የሚጠቀስ ነው። በተመሳሳይ ከGAGE, UNFPA እና UNWOMEN ጋር በመተባበር በሴቶችና ታዳጊ ሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃትን ለማስቆም የሚያስችሉ ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞች እንዲሁም ከሞሮኮ ጋር በመሆን የገጠር ሴቶችን በመደገፍ ዘላቂ የልማት ግቦችን ማሳካት ላይ ያተኮሩ መድረኮች ተካሂደዋል።

በዚሁ ጊዜም የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በተጠቀሱት ዘርፎች የኢትዮጵያን ጥረትና ስኬት በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት ገልጸዋል። የቤጂንግ መግለጫና የድርጊት መርሃ ግብር እ.ኤ.አ በ1995 በ11 ጉዳዮች ላይ ያተኮረና በዋነኝነት የስርዓተ ፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥ እና ሴቶችን ለማብቃት የወጣ ሰነድ ሲሆን መንግስታትና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት የስርዓተ ፆታ እኩልነት ለማረጋገጥ ሊወሰዱ የሚገባቸውን እርምጃዎችንም በዝርዝር የሚያስቀምጥ ፍኖተ ካርታ ነው፡፡ ሀገራት በየ5 አመቱ የድርጊት መርሐግብሩን አፈፃፀም ሁሉን አሳታፊ በሆነ መንገድ የሚገመግሙ ሲሆን ኢትዮጵያም ይህንን ግምገማ በ2017 ዓ.ም በማካሄድ ሪፓርቱን አቅርባለች።

በዘንድሮው ጉባኤም የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣ ማህበራዊ ከለላ፣ የሴቶች መሪነትና የውሳኔ ሰጪነት ተሳትፎ፣ በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት፣ የአካባቢ ጥበቃና የስርዓተ ፆታ አጀንዳዎች እንዲሁም የሰላምና ፀጥታ ጉዳዮችና ሌሎችም ትኩረት ተሰጥቷቸው በሰፊው ተዳሰዋል። በትልልቅ አጀንዳዎች ላይ ለቀናት ሲመክር የቆየው ጉባኤ የቀጣይ 5 ዓመት የቤጂንግ መግለጫ አፈፃፀምን ለማፋጠን የሚረዳ የማስፈፃሚ የድርጊት መርሐግብር በማፅደቅ ተጠናቋል።

በጉባኤው ላይ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድንን ጨምሮ የመንግስት ተወካዮች፣ ከተለያዩ የሲቪክ ማህበራት፣ የሴቶችና ወጣቶች ድርጅቶች፣ የጥናትና ምርምር ተቋማት፣ አለም አቀፍና አህጉራዊ ድርጅቶች የተጣውጣጡ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2025 ለሚካሄደው 70ኛው አለም አቀፍ የሴቶች ጉባኤ አፍሪካን በመወክል የኮሚቴው አባል ሆና መመረጧ ይታወሳል፡፡

Please follow and like us: