መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ለመከላከል እና መደበኛ ፍልሰትን ለማበረታታት የተዘጋጀ ብሔራዊ የኮምኒኬሽን ስትራቴጂና የጋራ የአምስት አመት መሪ እቅድ ይፋ ሆነ።

የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር እና አለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ለመከላከል እና መደበኛ ፍልሰትን ለማበረታታት የተዘጋጀ ብሔራዊ የኮምኒኬሽን ስትራቴጂና የጋራ የአምስት አመት መሪ እቅድ በዛሬው ዕለት በጋራ ይፋ አድርገዋል።

በዕለቱ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንደገለፁት መንግስት መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ለመቀነስና ዜጎች ክብራቸውና ደህንነታቸው ተጠብቆ በውጭ አገር የስራ ስምሪት እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ መንግስት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና አለም አቀፍ ተቋማት በትብብር መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ በዛሬው ቀን ይፋ የተደረጉት ብሔራዊ ኮምኒኬሽን ስትራቴጂና በሚኒስቴሩና በአለም ዓቀፉ የፍልሰት ድርጅት መካከል የተፈረመው የአምስት አመት መሪ እቅድ የፍልሰት አስተዳደርን ውጤታማና የተቀናጀ ምላሽ ለመስጠት፣ ህብረተሰቡን ማእከል ያደረገ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ማከናወን፣ የተጎጂዎችን ጥበቃና መልሶ ማቋቋም ስራዎችን ማጠናከር እና ለፖሊሲ አውጪዎች አስተማማኝ መረጃ ለማቅረብ፣ የፍልሰት መረጃን ለማደራጀትና ጥናትና ምርምር ለማድረግ የሚያስችሉ መሆኑን ሚኒስትሯ ጠቅሰዋል፡፡

በተጨማሪም ብሔራዊ የኮምኒኬሽን ስትራቴጂው መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት መከላከልና እና መደበኛ ፍልሰትን በማበረታታት፣ የፍልሰት መንስኤዎችንና የሚያስከትሉትን ችግሮች በማስገንዘብ የተሻሻለ የኑሮ አማራጮችን በማስተዋወቅ ላይ እንደሚያተኩር ጠቁመዋል። በዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት በኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቢባቱ ዋኔ-ፎል በበኩላቸው ዛሬ ይፋ የተደረጉት ሁለቱ ሰነዶች በቅንጅት በመስራት በፍልሰት አስተዳደሩ ውጤታማ ከማድረግ አንጻር ስኬትን የሚያስመዘግቡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

Please follow and like us: