የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ በቦሌ ሚካኤል የሚገኘው የስደት ተመላሽ ዜጎች ጊዜያዊ ማቆያ ማዕከል ጎበኙ

የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ በቦሌ ሚካኤል የሚገኘው የስደት ተመላሽ ዜጎች ጊዜያዊ ማቆያ ማዕከል ጎበኝተዋል።

ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ በጊዜያዊ ማቆያ ማዕከሉ እየተሰጡ ያሉ አገልግሎቶችንም ተዟዙረው ተመልክተዋል።

በተጨማሪም በአገልግሎት አሠጣጡ ዙሪያ ከተመላሽ ዜጎችና በመጠለያው አገልግሎት እየሰጡ ከሚገኙ አካላት ጋር ተወያይተዋል። ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ በዚሁ ጊዜም፥ በህጋዊ መንገድ ወደ ውጭ የሚሄዱ ዜጎች ደህንነታቸው፣ መብታቸውና ጥቅማቸው እንዲጠበቅ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል። የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ወደ ተለያዩ ሀገራት የሚሄዱ ዜጎችም መደበኛ ፍልሰትን ምርጫቸው በማድረግ ራሳቸውን ከተደራጁ ሕገ-ወጦች እንዲጠብቁ አስገንዝበዋል።

ሕገ-ወጥ ደላሎች ከህብረተሰቡ የተሸሸጉ አይደሉም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ሕገ-ወጦችን በማጋለጥ መንግስት ተገቢውን እርምጃ መውሰድ እንዲችል የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ድርጊቱን ከመከላከል ጎን ለጎን ከሚመለከታቸው ባለድርሻና አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት ለተመላሽ ዜጎች በአየር ማረፊያና በማቆያ ማዕከላት ተገቢውን ድጋፍ እና እንክብካቤ የማድረግ እና ከቤተሰብ ጋር የማቀላቀል ስራም እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡በቀጣይም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ያነሷቸውን አንዳንድ ችግሮች ለመፍታት ያላሰለሰ ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

በአጠቃላይ በውይይቱ ሕገ ወጥ ስደት አስከፊ መሆኑን፣ ዜጎች ሕገወጥ መንገድንን መምረጥ እንደሌለባቸው፣ መተላለፊያ ድንበሮች እንዲዘጉና በሕገወጥ ደላሎች ላይ ጠንካራ እርምጃ እንዲወሰድ ተመላሽ ዜጎች በሰጡት አስተያየት ገልፀዋል።ለተመላሾች አገልግሎት እየሰጡ ያሉ በጎ ፈቃደኞችና የሴክተር ባለሙያዎችን አድንቀው እያበረከቱ ላለው በጎ አስተዋፅዖ ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ አመስግነዋል።በዕለቱ ለተመላሽ ዜጎች የቴምር ስጦታ ተበርክቷል።

 

Please follow and like us: