ሚኒስቴሩ ድጋሚ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል 1ሺ ከረጢት የሴቶች የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ በስጦታ አበረከተ።

የሴቶችና ማህበራዊ ሚኒስቴር ድጋሚ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል 1ሺ ከረጢት የሴቶች የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ በልደታ ከ/ከተማ ለሚገኘው እድገት በስራ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ለሚገኙ ሴት ተማሪዎች በስጦታ አበረከተ።

በርክክብ ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስቴር ድኤታ ሁሪያ አሊ አሁን ላይ በሚስተዋለው የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም፣የዋጋ ውድነትና ጥራት አለመኖር ምክንያት ሴቶችና ሴት ተማሪዎች ለተለያዩ ችግሮች እየተጋለጡ መሆኑን ጠቅሰው በተለይም ከትምህርት ለማቋረጥና በተደጋጋሚ ከትምህርት ገበታቸው ለመቅረት እንደሚገደዱ ገልፀዋል። ይህ ችግር ደሞ በይበልጥ በገጠሪቱ የአገራችን ክፍል የሚታይና ለችግር ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይም ጎልቶ እንደሚታይ አስታውቀው በአገር ውስጥ ቴክኖሎጂ መመረቱ ይህን ችግር በዘላቂነት መፍታት ከማስቻሉም በላይ ለወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራም የራሱን በጎ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ጠቁመዋል ።

በዛሬው እለትም ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ቃል በገባው መሠረት ድጋሚ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል የሴቶች የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያን ከቱርክ የልማትና ትብብር ኤጀንሲ ጋር በትብብር በመሆን ለእድገት በስራ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች እንዳበረከተ ገልፀዋል። የንፅህና መጠበቂያው ጀረጃውን የጠበቀና ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የተመረተ በመሆኑን ተማሪዎች ያለስጋት እንዲጠቀሙበት አሳስበዋል።ሌሎች የአገር ውስጥ አምራች ድርጀቶችም በዘርፉ በመሠማራት ለነገ የሴት ልጆቻችን ዕድገት መቃናት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል ።

የቱርክ የልማትና ትብብር ኤጀንሲም በኢትዮጵያ በጤና በትምህርት በሰብአዊ ድጋፎችን ጨምሮ በተለያዩ ፕሮጀክቶች ለሚያደርገው አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበዋል። በድጋሚ ጥቅም ላይ የሚውለው የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ እስከ ሁለት አመት ድረስ የሚያገለግል ሲሆን በዛሬው ዕለትም የተበረከተው ስጦታ ለ1ሺ ተማሪዎችም ተደራሽ ይሆናል።

 

Please follow and like us: