Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
በተለያዩ ሀገራት በችግር ላይ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው የመመለስ የማቋቋምና ወደ አካባቢያቸው ለመመለስ የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክረን እንቀጥላለን -አቶ ጌታቸው በዳኔ (የሚኒስትር አማካሪ)
በተለያዩ ሀገራት በችግር ላይ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው የመመለስ የማቋቋምና ወደ አካባቢያቸው ለመመለስ የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር አማካሪ አቶ ጌታቸው በዳኔ ገለፁ።

ፍልሰተኞችን ለማዳን ወደ አካባቢያቸው ለመመለስ፣ መልሶ ለማቋቋም፣ ህገወጥ ፍልሰትን ለማስቀረትና መደበኛ ፍልሰትን ለማበረታታት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ይገኛል ብለዋል። የቅብብሎሽ አሰራርን ማጠናከር በሚቻልበት ዙሪያ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የሚመለከታቸው የክልል ቢሮ ሃላፊዎች የተካፈሉበት የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው። በመድረኩ ላይ መንግስት መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት እያስከተለ ያለውን ጉዳት በመገንዘብ በሰው የመነገድ፣ በህገ-ወጥ መንገድ ሰውን ድንበር ማሻገር እና ለስራ ወደ ውጭ ሀገር መላክ ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የህግ ማዕቀፎችን በማውጣት ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ለመከላከል የሚያስችሉ የማህበረሰብ ንቅናቄና የግንዛቤ ስራዎችን በማካሄድ በህብረተሰቡ ዘንድ የአመለካከት ለውጥ በማምጣት ችግሩን ከስረ-መሰረቱ የመቅረፍ ስራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል። አያይዘውም የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ተመላሽ ዜጎች ማህበራዊና ስነ-ልቦናዊ ድጋፍ እንዲያገኙ የማድረግ፣ ከፌዴራል እስከ ክልል ድረስ አስፈላጊ አደረጃጀቶችን በማቋቋም ምላሽ በመስጠት ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል። መድረኩ በተለይም በድሬዳዋ ከተማ የተዘጋጀበት ዓብይ ምክንያትም ድሬዳዋ በምስራቁ የመውጫ መስመር ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ፍልሰተኞች ከተለያዩ የሀገራችን ክፍል መደበኛ ባልሆነ መንገድ ወደ ጎረቤት ሀገርና ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ለመሄድ ለሚመጡ ፍልሰተኞች ማረፊያና መሸጋገሪያ ከሆኑት የሀገራችን አካባቢዎች አንዷ በመሆኑ ነው ብለዋል።

በዚህ መድረክ ተጎጂ ፍልሰተኞች ማዕከል በማድረግ የቅብብሎሽ አሰራሩን ለማጠናከር እና በአሰራሩ ላይ ያሉ ተግዳሮቶች ላይ በመወያየት የመፍትሄ ሃሳብ ይጠቁማል ተብሎ ይታመናል በማለት ገልጸዋል ገልፀዋል። የድሬዳዋ አስተዳደር ም/ከንቲባም ክቡር አቶ ሀርቢ ቡህ በበኩላቸው መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት ሰብዓዊ ክብርን የሚነፍግ ባለብዙ ፈርጅ የወንጀል ተግባር ነው ብለዋል፡፡ በሰዎች የመነገድ ድርጊት ራስን ለመጥቅም በሰዎች ላይ በሚፈፀም መጥፎና ጎጂ ተግባር፤ ከመነሻ እስከ መድረሻ በክፋትና በጭካኔ የተሞላና በሂደቱም ሞት፣ አካላዊና አዕምሯዊ ጉዳትን ሊያስከትል የሚችል የወንጀል ድርጊት እንደሆነም ገልፀው አስተዳደሩ ድርጊቱን ለመከላከል በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

ተሳታፊዎችም በቀጣይ ተጎጂ የሆኑ ከፍልሰት ተመላሽ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋምና ወደየ አካባቢያቸው ለመመለስ በሚያስችል በቅብብሎሽ አሰራር ዙሪያው በተጠናከረ መልኩ በቅንጅት መስራት እንደሚገባም ገልፀዋል። በዕለቱም መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት ያስከተላቸው ጉዳቶች፣ የተሰጡ መፍትሄዎችና ዜጎች መደበኛ በሆነ መልኩ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪትን መከተል በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ግንዛቤ እንዲጨብጡ ተደርጓል። በመድረኩም የሁሉም ክልል ማህበራዊ ዘርፍ ቢሮ አመራሮች የሚመለከታቸው የፌደራል ተቋማትና ከመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ ዓለም-ዓቀፍ የፍልሰት ድርጅት እና የህፃናት አድን ድርጅትተገኝተዋል ።
