በድሬዳዋ የሚገኘው የፍልሰት ተመላሾች ጊዜያዊ አገልግሎት መስጫ ማዕከል ተጎበኘ

በድሬዳዋ የተካሄደው ሀገር አቀፍ የብሔራዊ ቅብብሎሽ ሥርዓት ምክክር መድረክ መጠናቀቁን ተከትሎ ተሳታፊዎች የፍልሰት ተመላሾች ጊዜያዊ አገልግሎት መስጫ ማዕከል ጉብኝት አካሂደዋል።

የጉብኝቱ አላማም ተሳታፊዎች ከማዕከሉ ስራዎች ጋር በቀጥታ እንዲገናኙ በማድረግ የፍልሰት ተመላሾችን አቀባበል፣ የፈጣን ድጋፍ አገልግሎት፣ በተቋማቱ መካከል ያለውን ቅንጅት አሠራር እና ምላሽ አሰጣጥ ሂደትን የበለጠ እንዲረዱና ተሞክሮ እንዲወስዱ ለማስቻል ነው ተብሏል። ማዕከሉ ከተለያዩ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ከሳዑዲ ዓረቢያ፣ ከየመን እና ሌሎችም ሀገራት የሚመለሱ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች የመጠለያ፣ የምግብ፣ የጤና እና የስነ-ልቦናና ማህበራዊ ድጋፍ እንዲሁም ተመላሾችን ወደ አካባቢያቸው የማቀላቀልና የመልሶ ማቋቋም ስራዎች እንደሚያከናውንም ተገልጿል።

በጉብኝቱ ወቅት የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አብዱራህማን ሙሳ ምላሽ መስጫ ማዕከሉ ለአደጋ የተጋለጡ ፍልሰተኞችን በመጠበቅ እና ወደ አካባቢያቸው መልሶ በማቀላቀል ረገድ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ይገኛልም ብለዋል። አብዛኛዎቹ ፍልሰተኞች በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነው የተመለሱ መሆናቸውንም አብራርተዋል። ማዕከሉ እያደገ የመጣውን የተመላሾችን ፍላጎት ለማሟላት ያለውን አቅም ለማጠናከር የመንግስት፣ የግል፣ የበጎ አድራጎት እና አለም አቀፍ ድርጅቶች ትብብርና ቅንጅት አስፈላጊ መሆኑን በመጠቆም ቀጣይነት ያለው ኢንቨስትመንት እንዲጠናከርም ጠይቀዋል።

ጉብኝቱ ከፍልሰት ተመላሾች በተለይ ሴቶች፣ ህጻናት እና ሌሎች ተጋላጭ የማህረሰብ ክፍሎች ወቅታዊ እና ሁሉ ዓቀፍ ድጋፍ የሚያገኙበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የብሔራዊ ቅብብሎሽ ሥርዓቱን ለማጠናከር ጎልህ ሚና እንደሚኖረው የጉብኝቱ ተሳታፊዎች ገልፀዋል።

Please follow and like us: