Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የቤተሰብን የኢኮኖሚ ተጋላጭነት ለመቀነስ ያለመ የምክክር መድረክ ተካሄደ
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የቤተሰብን የኢኮኖሚ ተጋላጭነት ለመቀነስ ያለመ ውይይት ከባለድርሻ አካላት ጋር አካሂዷል።

የሚኒስቴሩ የአረጋዊያንና ቤተሰብ ጉዳዮች ስራ አስፈጻሚ አቶ ተስፋዬ ሮበሌ ቤተሰብ በተነቃቃ የስራ ባህል ጥሪት በማፍራትና ኢኮኖሚውን በመገንባት ከራስ ባለፈ ለማህበረሰብ ሁለንተናዊ ለውጥ ብሎም ለሀገር ግንባታ የጎላ አስተዋፅፆ ያበረክታል ብለዋል። ሆኖም በተለያዩ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት ቤተሰብ ለልዩ ልዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተጋላጭ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ቤተሰብ ያለውን ሚና ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በመሆኑም አጋላጭ ምክንያቶችን በጥናት በመለየት ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመቅረፍና የቤተሰብን ደህንነት ለማረጋገጥ ብሎም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙትን በዘላቂነት ለማቋቋም በትብብር መስራት እንደሚገባ ስራ አስፈፃሚው አስገንዝበዋል። ለዚህም በተለይ በቤተሰብ ዙሪያ የሚሰሩ ባለድርሻና አጋር አካላት ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጡና ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል። በመድረኩ የቤተሰብ የኢኮኖሚ ተጋላጭነት ለመቀነስ እንዲያስችል የተዘጋጀ ሰነድን ጨምሮ ሀገር አቀፍ የእድሮች ጥምረት ምክር ቤት በኩል የቤተሰብን ጉዳይ ማዕከል አድርገው ሊከናወኑ በሚገባቸው ተግባራት ዙሪያ ሰነድ ቀርቦ ምክክር ተካሂዷል።

በቀጣይም ተቀናጅቶና ተናቦ ከመስራት አኳያ ያሉ ጅምሮችን አጠናክሮ በማስቀጠል፣ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በመፍታትና አስቻይ ሁኔታዎችን በሚገባ በመጠቀም በዘርፉ የሚጨበጥ ለውጥ ለማምጣት በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ በተቀመጠው አቅጣጫ ላይ የጋራ መግባባት ተፈጥሯል። በመድረኩ ከሐይማኖት ተቋማት ህብረት እና ከማህበረሰብ አቀፍ አደረጃጀቶች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
