በግዳጅ ተፈናቅለው የተመለሱ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተገለፀ

በሱዳን በተከሰተው የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት ተፈናቅለው የተመለሱ ዜጎችን መልሶ ማቋቋም ላይ ትኩረት ያደረገ የፖሊሲ ምክክር እየተካሄደ ይገኛል።

በመድረኩ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አሳልፈው አህመዲን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ከመከላከል ጎን ለጎን ለተመላሽ ዜጎች የማህበራዊ፣ ስነልቦናዊና ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ እና እንክብካቤ እንዲያገኙ የማድረግና ከቤተሰብ ጋር የማቀላቀል ስራ በቅንጅት እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡ በግዳጅ ተፈናቅለው የተመለሱ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም በትብብር መስራት እንደሚገባ ገልፀዋል።

መድረኩ በዋናነት በተለያየ ምክንያት ከመደበኛ ህይወታቸው በግደጅ የሚፋናቀሉ ዜጎች ልዩ ልዩ ድጋፍ ስለሚያገኙበት እና ከህብረተሰቡ ጋር ሊቀላቀሉ ስለሚችሉበት ሁኔታ ለመሞከር ያለመ መሆኑን አንስተዋል። ባለድርሻ አካላት ሊከተሉት ስለሚገባ የፖሊሲ አቅጣጫዎች እንዲሁም በመካከላቸው ሊኖር ስለሚገባው ቅንጅታዊ አሰራር በመምከር የቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ መድረኩ መዘጋጀቱንም አስገንዝበዋል፡፡

የብሔራዊ ትብብር ጥምረት ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ አብርሃም አያሌው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ በተፈጥሮና በሠው ሠራሽ ምክንያቶች ተገደው የሚፈልሱ ፍልሰተኞች መነሻ፣ መተላለፊያ መዳረሻ ሀገር መሆኗን ተግረዋል። ችግሩን ለመቅረፍ መንግስት የአደረጃጀት፣ የህግና የአሰራር ማዕቀፍ መዘርጋቱንና አለም አቀፍ ስምምነቶችን በመፈረም በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል።

 

የአለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት (IOM) ተወካይ ማዳም ሚሞሪ መዋሌ በበኩላቸው በግዳጅ መፈናቀልን ጨምሮ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት በኢትዮጵያና በአጠቃላይ አፍሪካ ቀንድ አካባቢ እያስከተለ ያለውን የሰብአዊ ቀውስ ለመቀነስ በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ እገዛ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።

የምክክር መድረኩ የፍትሕና የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከአለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን በመድረኩ የተለያዩና የፌዴራልና የክልል ተቋማት፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት፣ የአለም አቀፍ ድርጅት ተወካዮች እንዲሁም ከስደት ተመላሽ ዜጎች ተገኝተዋል።

Please follow and like us: