Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
አሳሳቢ ደረጃ ላይ የሚገኘው ህገወጥ የሰዎች ዝውውር እና መፍትሔው
ዜጎች ለስራና ለተሻለ ህይወት ፍለጋ ሲባል ከቦታ ቦታ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ተፈጥሯዊና ህገ-መንግስታዊ መብት ነው። እውነታው ይህ ቢሆንም በደላሎች ተታለው ከሃገር ለመውጣት የሚጥሩ ወጣቶች፣ ሴቶችና ታዳጊ ህፃናት ቁጥር እየተበራከተ መምጣቱ ሁኔታውን እጅግ አሳሳቢ ያደረገዋል። በየጊዜው ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ዜጎች በህገወጥ መንገድ ከሀገር ሊወጡ ሲሞክሩ በድበር ጠባቂዎችና ሌሎች የተደራጁ አካላት እጅ እየወደቁ ከፍተኛ ለሆነ የጤና፣ የአእምሮ፣ የስነ-ልቦና፣ የአካል ጉዳትና ለሌሎች ተደራራቢ ችግሮች ሲዳረጉ በስፋት ይስተዋላል። የዝውውር ሂደቱ በተለይም ደግሞ ለሴቶች እና ህፃናት ከባድ እንደሆነም መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ደህንነቱ በልተጠበቀና አስተማማኝ ባልሆነ ጉዞ ላይ በሚገጥመው እንግልትም የብዙዎች ህይወት እስከ ማለፍ እንደሚደርስ በየዕለቱ የምንሰማው አሳዛኝ ዜና ሆኗል። በቅርቡ በጂቡቲ ባህር ዳርቻና በሌሎችም መተላለፊያዎች የተከሰተው አደጋ ለዚህ ትልቅ ማሳያ ነው፡፡ መንግስት እያካሄደ ባለው ዜጋ ተኮር የዲፕሎማሲ ስራ ካለፈው ሚያዚያ ወር ጀምሮ በተለይ በሳዑዲ ዓረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ወስጥ የነበሩ ከ82 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገር መመለሱ ሌላኛው ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ያስከተለው አሉታዊ ውጤት መሆኑን ልብ ይሏል። ድርጊቱ በሀገሪቱ ገፅታ ላይም የሚያሳድረው ተፅዕኖ እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
በጉዳዩ አሳሳቢነት ዙሪያ ግንዛቤ ለመፍጠር ሰፊ ጥረት እየተደረገና ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ቢሆንም ዛሬም በህገወጥ መንገድ የሚደረግ ፍልሰትና ስደት እንደቀጠለ ይገኛል። ታዲያ ዜጎች በኢኮኖሚያዊ ሁኔታ፣ በግንዛቤ ማነስ፣ በአቻ እና በቤተሰብ ግፊት ምክንያት አሊያም በተደራጁ የወንጀል ቡድኖች ተታለው ለህገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባ እየሆኑ የሚቀጥሉት እስከመቼ ድረስ ነው?
እንደሚታወቀው በሀገራችን በሰው መነገድ፣ ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር እና በህገ ወጥ መንገድ ሰውን ለስራ ወደ ውጭ ሀገር መላክ ድርጊት ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 1178/2012 መሠረት ተግባሩ የወንጀል ድርጊት መሆኑ በግልፅ ተደንግጓል።
ዓላማውም ብዝበዛና ትርፍ ማግኘት ላይ ያተኮረ እንጂ የዜጎችን ህይወት ለመለወጥ ታስቦ በቀናዒነት የሚከወን ድርጊት እንዳልሆነ መላው ህብረተሰብ በተለይም ደግሞ የሀገራችን ሴቶችና ወጣቶች በውል መገንዘብና አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
ውድ የሀገራችን ሴቶችና ወጣቶች – በሀገር ውስጥ ሰርቶ መለወጥ ይቻላል። ለዚህም የአመለካከት ለውጥ ማምጣት፣ ያሉትን ዕድሎችና መልካም አጋጣሚዎች አሟጦ መጠቀም፣ ትዕግስትን መላበስ፣ ተስፋ አለመቁረጥ፣ ስራን አለመናቅና ተግቶ መስራት ያስፈልጋል።
በአንፃሩ ውጭ ሀገር ሄዶ መስራት ግድ ከሆነ መደበኛና ህጋዊውን መንገድ መከተል፤ ለዚህ ደግሞ ትክክለኛውን መረጃ ከሚመለከተው አካል ብቻ መውሰድ እንደሚገባ አጥብቀን እንመክራለን።
እንደአጠቃላይ ግን መደበኛ ፍልሰትን ለመከላከልና በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ምክንያት በየጊዜው እያደረሰ ያለውን እንግልትና ሞት ለመቀነስ ራሳቸው ሴቶችና ወጣቶችን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻና አጋር አካላት በቅንጅት እንዲረባረቡ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥሪውን ያቀርባል፡፡ ህገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በአፅዕኖት ለማሳሰብ ይወዳል። በቀጣይም መንግስት በእነዚህ ግለሰቦች ላይ ጠንካራ እርምጃ መወሰድ እንዲችል ህብረተሰቡ ጥቆማ በመስጠት የበኩሉን ትብብር እንዲያደርግ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መልዕክቱን ያስተላልፋል።
