‎የዜጎችን ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍና በህይወታቸው ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት በቅንጅት መስራት ይጠበቅብናል – ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ

‎ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ አመታዊ የሴክተር ጉባኤ በስኬት ተጠናቋል።
‎
‎በጉባኤው የ2017  አፈፃፀም እና የቀጣይ እቅድ ቀርቦ ሰፊ ውይይት የተካሄደ ሲሆን ከጉባኤተኛው ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በበላይ አመራሩ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል።
‎
‎በውይይቱ በየዘርፉ ያሉ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመፈተሽ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ አንኳር ጉዳዮችን በመለየት ጉባኤው የቀጣይ አቅጣጫ አስቀምጧል።
‎
‎በጉባኤ ማጠቃለያ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበጀት አመቱ በሴክተሩ ተደራሽ የሆኑትን የህብረተሰብ ክፍሎች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ በርካታ ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀዋል።
‎
‎የተገኘው ውጤት በየደረጃው የሚገኙ አስፈፃሚ አካላት ድምር ውጤት መሆኑንም በመግለፅ ምስጋና አቅርበዋል።
‎
‎ሆኖም የዜጎችን ችግር በዘላቂነት ከመቅረፍና በህይወታቸው ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ከማምጣት አኳያ በቀጣይ ብዙ መስራት ይጠበቅብናል ሲሉም ተናግረዋል።
‎
‎በቀጣዩ በጀት አመት የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት ያሉት ክብርት ሚኒስትሯ ሴክተሩ የተጣለበትን ሃላፊነትና ሚና በሚገባ መወጣት እንዲችል ይበልጥ ተናቦና ተቀናጅቶ መስራት እንደሚገባ በአፅኖኦት አሳስበዋል።
‎
‎እንደሴክተር የአፈፃፀም ወጥነት እንዲኖር፣ በመረጃ አያያዝና ልውውጥ፣ በመዋቅርና አደረጃጀት፣  በእውቀትና ክህሎት ረገድ ያሉትን ክፍተቶች ለመፍታት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
‎
‎ፈፃሚውን ለማብቃት የአቅም ግንባታ ስራዎችን፣ የድጋፍና ክትትል ተግባራትን እንዲሁም የግብረ መልስ አሰጣጥ ስርዓትን የበለጠ የማጠናከር ስራ ይሰራል ብለዋል።
‎
‎በአካቶ ትግበራ ረገድም የታየውን ጅማሮ የበለጠ በማጠናከር ተጠያቂነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል። ሁነቶች ውጤት ማምጣት በሚያስችል አግባብ መከወን እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
‎
‎በዕለቱ የ2018 በጀት ዓመት የሴክተር እቅድ የውል ስምምነት ፊርማ መርሐግብር ተከናውኗል።
‎

Please follow and like us: