በሳዑዲ ዓረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ዜጎችን ወደ ሀገር የመመለስ ስራ መጀመሩ ተገለፀ

በሳዑዲ ዓረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ዜጎችን ወደ ሀገር የመመለስ ስራ መጀመሩን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ ገለፁ።
‎‎መንግስት እየተከተለ ባለው ዜጋ ተኮር የዲፕሎሚሲ ፖሊሲ መሰረት በዓረብ ሀገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሀገር የመመለሱ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅትም በሳዑዲ ዓረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገር የመመለስ ስራ ከትናንት ሰኞ መስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን በመጀመሪያው ዙር መቶ ወንዶችን ወደ ሀገር መመለስ መቻሉን ጠቅሰዋል። ‎ለተመላሽ ዜጎች በአየር ማረፊያና በማቆያ ማዕከላት ተገቢውን ድጋፍ እና እንክብካቤ ከማድረግ ጎን ለጎን ከቤተሰብ ጋር የማቀላቀል ስራም እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡ ‎በዚህም ዙር 25 ሺህ ዜጎችን ከሳዑዲ ዓረቢያ ለመመለስ እቅድ መያዙንና ለዚህም በሳምንት ሶስት ቀን በየቀኑ ሶስት ጊዜ በሚደረግ በረራ ዜጎችን የመመለሱ ስራ የሚቀጥል መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠቁመዋል። ሚኒስቴሩ በህገወጥ የሰዎች ዝውውር አስከፊነት ዙሪያ ህብረተሰቡን ለማስገንዘብ፣ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ለመከላከልና ደህንነቱ የተጠበቀ ፍልሰትን ለማበረታታት የሚያስችሉ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

‎‎መደበኛ ባልሆነ ፍልሰት ወደ ተለያዩ ሀገራት ሄደው የሚመለሱ የፍልሰት ተጎጂዎችን ለመደገፍና መልሶ ለማቋቋምም በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል። በተለያዩ ጊዜያትም ከሚመለከታቸው ባለድርሻና አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት ለተመላሽ ዜጎች በአየር ማረፊያና በማቆያ ማዕከላት ተገቢውን ድጋፍ እና እንክብካቤ የማድረግ እና ከቤተሰብ ጋር የማቀላቀል ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

Please follow and like us: