Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የሀገር ባለውለታ አረጋውያን ቀሪ ዘመናቸውን በክብር እንዲያሳልፉ መደገፍና መንከባከበ ከሁሉም ይጠበቃል
በአረጋውያን መብትና ተጠቃሚነት ዙሪያ የባለድርሻና አጋር አካላትን ግንዛቤና ምላሽ ሰጪነት ሚና ለማሳደግ ያለመ የምክክር መድረክ ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ተካሂዷል።
በመድረኩ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአረጋውያንና ቤተሰብ ጉዳይ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተስፋዬ ሮበሌ፥ ከሉላዊት፣ ከከተሞች መስፋፋት፣ ከእድሜና ከተለያዩ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ክስተቶች ጋር በተያያዘ አረጋውያን ለከፋ ችግር ሲጋለጡ ይስተዋላል ብለዋል። አረጋውያን በጉብዝና ዘመናቸው ይብዛም ይነስም ለሀገር ብዙ የሰሩ ባለውለታ በመሆናቸው ተገቢው ፍቅር፣ ድጋፍና ክብካቤ እያገኙ ቀሪ እድሜያቸውን በክብር እንዲያሳልፉ ማስቻል ከሁሉም ይጠበቃል ብለዋል። ሚኒስቴሩ የአረጋውያንን ጉዳይ በአስፈፃሚ አካላት እቅድ ውስጥ እንዲካተት፣ ተገቢው ምላሽ እንዲሰጠውና መብትና ደህንነታቸው እንዲጠበቅ ለማድረግ በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል። በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የክልል ከተሞች የአረጋውያን ማዕከላትን የመገንባትና የማስፋፋት ሥራዎች እየተሠሩ ቢሆንም፥ በሀገሪቱ ውስጥ ካለው የአረጋውያን ቁጥር አንፃር በቂ አለመሆኑን ተናግረዋል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በወረዳ ደረጃ የአረጋውያን መንከባከቢያ ማዕከል ለመገንባት መታቀዱን ጠቁመው ለስኬታማነቱ የሁሉም አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል። በተያያዘም አለም አቀፉ የአረጋውያን ቀን ዘንድሮ በሀገራችን ለ34ኛ ጊዜ “ለአረጋውያን ደህንነት መጠበቅ ሁለንተናዊ ሃላፊነታችንን እንወጣ” በሚል መሪ ቃል በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚከበር አስታውቀዋል። በአረጋውያን መብቶችና ተጠቃሚነት ዙሪያ ግንዛቤን በማስረፅ ሁሉም ተግባራዊ ምላሽ እንዲሰጥ በማስቻል ረገድ መገናኛ ብዙሃን ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
