ጠንካራ የፍልሰት አስተዳደር ለመዘርጋት፣ ደህንነቱ የተጠበቀ ፍልሰትን ለማበረታታትና ተፈናቃዮችን ለመደገፍ የሚያስችል የአምስት አመት ስትራቴጂክ እቅድ ይፋ ሆነ

አለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት/IOM/ በኢትዮጵያ ጠንካራ የፍልሰት አስተዳደር ለመዘርጋት፣ ደህንነቱ የተጠበቀ ፍልሰትን ለማበረታታትና ተፈናቃዮችን ለመደገፍ እንዲያስችል ያዘጋጀው የአምስት አመት ስትራቴጂክ እቅድ በዛሬው ዕለት ይፋ ሆኗል።

‎በመርሐግብር ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ፥ በተለያዩ ገፊና ሳቢ ምክንያቶች በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች መደበኛ ባልሆነ መንገድ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ተናግረዋል።‎‎ኢትዮጵያ መደበኛ ያልሆኑ ፍልሰት መነሻ፣ መተላለፊያና መዳረሻ ሀገር በመሆኗ ከፍልሰት ጋር በተያያዘ ዘርፈ-ብዙ ተግዳሮቶችን እየተጋፈጠች እንደምትገኝ አንስተዋል።‎‎መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት ዜጎችን ለበርካታ ጉዳቶች እየዳረጋቸው ይገኛል ያሉት ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ፥ ሚኒስቴሩ ችግሩን ለመከላከልና ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

‎በዛሬው እለት ይፋ የተደረገው ስትራቴጂክ እቅድም መንግስት በዘርፉ ካስቀመጠው የአስር አመት እቅድ ጋር የሚጣጣምና ቀደም ሲልም በቅንጅት የሚሰሩ ተግባራትን የበለጠ ለማጠናከር የጎላ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል። ‎ለውጤታማ ትግበራም ሚኒስቴሩ በጋራ እንደሚሰራና የድርሻውን እንደሚወጣ አስታውቀዋል። የዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ አቢባቱ ዋኔ፤ የፍልሰተኞች ጉዳይ በዓለም አቀፍ ደረጃ አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ ችግሩን ለመቅረፍ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው ስትራቴጂክ እቅዱ ይፋ መደረጉም የዚሁ ጥረት ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።‎

ስትራቴጂክ እቅዱ በዋነኛነት በፍልሰት ላይ የሚገኙ ዜጎች ጥበቃና ህይወት አድን ድጋፎችን ማድረግ፣ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን ለማቋቋምና ወደ ቀያቸው ለመመለስ እና መደበኛ የሆነ የፍልሰት ስርዓትን በማበረታታት መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን መከላከል ላይ ያተኮረ ፍኖተ ካርታ መሆኑን ገልፀዋል። ‎ስትራቴጂክ እቅዱ እ.ኤ.አ ከ2025-2029 እንደሚቆይ ለማወቅ ተችሏል።

‎

Please follow and like us: