መንግስት ለገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ውጤታማነትና ለዜጎች የተሻለ ተጠቃሚነት ከፍተኛ ሀብት በመመደብ በትኩረት እየሰራ ይገኛል – ክብርት ሁሪያ አሊ

መንግስት ለገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ውጤታማነትና ለዜጎች የተሻለ ተጠቃሚነት ከፍተኛ ሀብት በመመደብ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ ገለፁ።

‎ሚኒስቴሩ በፕሮግራሙ በቋሚና በጊዜያዊ የቀጥታ ድጋፍ የሚሠጡ አገልግሎቶችን ውጤታማነትን እና የዜጎችን የተሻለ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ያለመ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል። ‎የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ መንግስት በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ምክንያት ለተለያዩ ለማህበራዊና ኢኮኖሚ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ ዜጎችን ለመደገፍ የሚያስችል ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም በመቅረፅና ከፍተኛ ሀብት በመመደብ በትኩረት እየሰራ ይገኛል። ‎ባለፉት 5 የፕሮግራሙ ትግበራ አመታትም በገንዘብ ድጋፍና በመሰረታዊ የማህበራዊ አገልግሎቶች ትስስር መፍጠር ረገድ መጠነ ሰፊ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰው በዚህም በርካታ ወገኖችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል። በራስ አቅም ፕሮግራሙን ለማስቀጠል፣ የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካና ዜጎችም የተሻለ ተጠቃሚነት እንዲሆኑ ለማስቻል በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

‎ዘርፉን በእውቀት መምራት፣ የተጀመሩ ስራዎችንም የበለጠ አጠናክሮ ማስቀጠል እና በተሻለ አቅም የተሻለ አገልግሎት መስጠት ከፈፃሚ አካላት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። ለፕሮግራሙ ትኩረት እንዲሰጡ፣ በቅንጅት እንዲሰሩና በስልጠናው ያገኙትንም ክህሎት በአግባቡ በስራ ላይ እንዲያውሉ ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ በአፅዕኖት አሳስበዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን እገዛና ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።
‎
‎ስልጠናው በዋናነት መሠረታዊ የማህበራዊ አገልግሎት ትስስርን በማጠናከር፣ የማህበራዊና ስነልቦናዊ ድጋፍ አገልግሎት እና በጉዳይ አያያዝ ዙሪያ ባሉ የአሰራር ማዕቀፎች ላይ ያተኮረ ነው። በስልጠና መርሐግብሩ ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ጤና መድን ድርጅት እንዲሁም ከኦሮሚያ፣ ከድሬደዋ፣ ከትግራይና ከሐረሪ ብሔራዊ ክልሎች የተውጣጡ የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ጽ/ቤት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛል።
‎

Please follow and like us: