Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ለሴቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለፀ
የሴቶች ኢኮኖሚ ማብቃት ብሔራዊ ስትራቴጂ ዝግጅት ላይ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ እየተካሄደ ነው::
በመድረኩ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሂክማ ኸይረዲን፥ መንግስት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም ማካሄዱን ተከትሎ ለውጦች መመዝገባቸውንና በሂደቱም የሴቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል። በተካሄደ ሰፊ የንቅናቄ ስራ በህብረት ስራ ማህበራት የተደራጁ ሴቶች ከ27 ቢሊዮን ብር በላይ መቆጠብ መቻላቸውን ገልፀዋል። የገጠር ሴቶች በተናጠልና በጋራ በመሆን ግብርናን ማዕከል ባደረጉና በሌሎችም መስኮች በመሰማራት የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛል ብለዋል። ይሁንና አሁንም የብድር፣ የዋስትና፣ የመስሪያ ቦታ፣ የክህሎትና መሠል ችግሮች መኖራቸው ለሴቶች የኢኮኖሚ ተሳትፎና ተጠቃሚነት መረጋገጥ ማነቆ ስለመሆናቸው አንስተዋል።
ሚኒስቴሩ የሴቶች ፖሊሲ ክለሳ እና የስርዓተ ፆታ እኩልነትና ማብቃት ፖሊሲ ዝግጅትን እየተጠናቀቀ መሆኑንና ሌሎች ደጋፊ የአሰራር ማዕቀፎች እንዲቀረፁና በስራ ላይ እንዲውሉ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፥ ለሴቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል። ዩኤን ውመን/UNWOMEN/ በሴቶች የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ዙሪያ የሚሰሩ ባለድርሻ አካላትን ያቀፈ ፎረም ከማቋቋም በተጨማሪ ለስትራቴጂው ዝግጅት ላበረከተው የላቀ አስተዋፅዖ ምስጋና አቅርበዋል። ስትራቴጂው እንደሀገር የሴቶች የኢኮኖሚ ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት እና የላቀ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት ውጤታማ እንዲሆን የበኩሉን አገዛ እንደሚያደርግ ያላቸውን እምነት ገልፀው ለተግባራዊነቱ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የዩኤን ውመን ኢትዮጵያ ሀገራዊ ፕሮግራም ተወካይ ሚስተር ሻድራክ ዱሳቤ በበኩላቸው፥ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለሴቶች መብት መከበር፣ ለስርዓተ ፆታ እኩልነትና ሴቶችን ለማብቃት የተጓዘውን ርቀትና የተገኘውን ውጤት አድንቀዋል። በቀጣይም ዩኤን ውመን ሴቶችን በኢኮኖሚ ለማብቃት የተጀመሩ ስራዎችን ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል በጋራ እንደሚሰራና ድጋፍም እንደሚያደርግ ገልፀዋል።
