Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
በሕፃናት ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት ማስቆም የተቀናጀ እርምጃ፣ ወጥ የሆነ ኢንቨስትመንት እና ቆራጥ አመራር ይፈልጋል- ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ
በዓለም ዓቀፍ ደረጃ እ.ኤ.አ 2024 በኮሎምቢያ ቦጎታ በሚንስትሮች ደረጃ በዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ በህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን መከላከልና ምላሽ መስጠት ላይ በተከናወኑ ተግባራት ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደገለፁት፥ ከቦጎታ ቃልኪዳን በኃላ የኢትዮጵያ መንግስት የቅድመ ልጅነት እድገት እንክብካቤ ማዕቀፍ (NCF) በ2030 ከነበረበት 15% ወደ 50% ለማስፋፋት አቅዶ አሁን ላይ ሽፋኑ 19% መድረሱን ገልፀዋል። የህፃናት ጥበቃ ጉዳይ አስተዳደር ማዕቀፍን ከነበረበት 2% ወደ ወደ 6% ከፍ ማለቱን ጠቅሰው ይህም ለሀገራዊ እና ለአህጉራዊ ግቦቻችን አበረታች እድገት መሆኑን ጠቅሰዋል። በተጨማሪም የልጅነት ጋብቻን እና የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም የሚያስችል መደበኛ በጀት እና የወጪ ክትትል ስርዓት ለማቋቋም ማህበረሰቡን ያካተቱ ትብብሮች እንደተጀመሩ ጠቅሰዋል። እነዚህ ስኬቶች የኢትዮጵያን የቦጎታ ቃልኪዳኖችን እውን ለማድረግ እና እያንዳንዱ ልጅ በደህንነት፣ በክብር እና በተስፋ እንዲያድግ ያላትን ጽኑ ቁርጠኝነት በጉልህ ያንፀባርቃል ብለዋል።
ምንም እንኳን ከቦጎታ ቃልኪዳን በኃላ በአህጉሪቱ ጉልህ የሆነ እድገት ቢገኝም፣ አሁንም ተግዳሮቶች መኖራቸውን አንስተዋል። ለአብነትም ግጭት፣ መፈናቀል፣ ድህነትና በአየር ንብረት ምክንያት የሚከሰቱ ቀውሶች በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአፍሪካ ሕፃናትን ለጥቃትና ለብዝበዛ ተጋላጭ እያደረጋቸው መሆኑን ጠቅሰዋል። ይህ ኮንፈረንስም እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የለውጥ መነሻ መሆን እንዳለበት ጠቅሰው የጋራ ቁርጠኝነታችንን ለማደስ እና ቃል ኪዳኖቻችንን ሊለኩ ወደ ሚችሉ እርምጃዎች ለመተርጎም በትብብር መስራት አለብን ሲሉ ተደምጠዋል። በሕፃናት ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት ማስቆም የተቀናጀ እርምጃ፣ ወጥ የሆነ ኢንቨስትመንት እና ቆራጥ አመራርን ደፈልጋል ብለዋል።
ለዚህም በመንግሥታት፣ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ በግሉ ዘርፍ እና በማኅበረሰቦች መካከል ዘላቂ የሆነ ትብብር መፍጠርና በጋራ መስራት ይገባል ብለዋል። በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ምክትል ተወካይ ዶ/ር አቡበከር ካምፖ በበኩላቸው፥ የኒሴፍ ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን ኢትዮጵያን ጨምሮ የህፃናትን ጥቃት ለማስቀረት የሚደረገውን አህጉራዊ እንቅስቃሴ እንደሚደግፉ አስታውቀዋል።
