‌‎ኢትዮጵያ በገባችው የቦጎታ ቃል ኪዳን መሠረት በህፃናት ጥቃት መከላከል ዙሪያ ለሰጠችው ቁርጠኛ ፖለቲካዊ አመራርና ለተገኘው አበረታች ውጤት አህጉራዊ እውቅና አገኘች

‎”Advancing the Bogota’ Commitments to End Violence Against Children In Africa” በሚል መሪ ቃል የህፃናት ጥቃት መካላከል ላይ ያተኮረ ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው።

‎‎የህፃናት ጥቃትን በመከላከል ረገድ የላቀ ስራ ለሰሩ የአፍሪካ አገራት የእውቅና መርሐግብር ተካሂዷል። ኢትዮጵያ በገባችው የቦጎታ ቃል ኪዳን መሠረት የህፃናት ጉዳይ አያያዝ ስርዓትን ለማስፋፋት፣ ለማዘመንና ለማጠናከር፣ የሴት ልጅ ግርዛትና ያለዕድሜ ጋብቻን ለመቀነስ እንዲሁም የቀዳማይ ልጅነት እድገት ስራዎችን ለማጠናከር ብሎም የቤተሰብ የህፃናት አያያዝና አስተዳደግ ላይ ግንዛቤና ተጠቃሚነት ለማሳደግ ለሰጠችው ጠንካራ አመራርና ለተገኘው ውጤት አህጉራዊ እውቅና አግኝታለች። ‎የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፥ ሕጻናት መብታቸው እንዲከበር ከማንኛውም አይነት ጥቃት መከላከል ምርጫ አሊያም ውዴታ ብቻ አይደለም፤ ሃላፊነታችንና ግዴታችንም ጭምር ነው ብለዋል። ‎ለዚህም ኢትዮጵያን ጨምሮ የህፃናትን ጥቃት ለመከላከልና ለማስቀረት በርካታ ጥረቶች እየተደረጉና አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆናቸው አስታውቀዋል።

‎የተሰጠው እውቅና ለላቀ አፈፃፀም እንደሚያነሳሳ፤ በኮንፈረንሱ የሚደርስባቸው ድምዳሜዎችም በቀጣይ ለሚሰሩ ስራዎች አቅም እንደሚሆኑ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል። ‎የህፃናት ጥቃት መከላከል ጉዳይ ከንግግር ያለፈ ገቢራዊ እርምጃ ስለሚሻ ሁላችንም መልካም ተሞክሮዎችን በማስፋፋት ለበለጠ ውጤታማነት መትጋት ይኖርብናል ብለዋል። ‎ኮንፈረንሱ የተዘጋጀው የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዩኒሴፍ፣ ከአለም ጤና ድርጅት እና ከአፍሪካ ቻይልድ ፖሊሲ ፎረም ጋር በመተባበር ነው። ‎በኮንፈረንሱ ለመታደም ከ35 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ሚኒስትሮች፣ የአለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች፣ የጥናትና ምርምር ተቁዋማት : የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች እና ታዳጊ ህፃናት ተገኝተዋል።

Please follow and like us: