Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የሴቶችን ውሳኔ ሰጪነት ሚና ለማሳደግና ተተኪ አመራሮችን ለማፍራት የሚከናወኑ ተግባራት ይቀጥላሉ
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ዩ ኤን ውሜን /UNWomen/ በጋራ በመሆን ያዘጋጁት ተተኪ ሴት አመራሮችን ለማፍራት ያለመውና ለ10 ተከታታይ ቀናት ሲሰጥ የቆየው 2ኛው ዙር የአቅም ግንባታ ስልጠና ተጠናቋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚኒስትር አማካሪ የሆኑት አቶ ሰለሞን አስፋው በመርሐግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ሴቶች በሁሉም መስክ እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ በርካታ ጥረቶች እየተደረጉና አበረታች ውጤቶችም እየተመዘገቡ መሆኑን ገልፀዋል።
ሆኖም ሴቶች በውሳኔ ሰጪነት ረገድም ሆነ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ዘርፍ ውስጥ ያላቸው ተሳትፎና ተጠቃሚነት በሚፈለገው ደረጃ ላይ እንዲደርስ ብዙ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል። የሴቶችን ውሳኔ ሰጪነት ሚና ለማሳደግና ተተኪ አመራሮችን ለማፍራት የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል። የአቅም ክፍተትን ለመሙላት ስልጠናው የበኩሉን እገዛ ያደርጋል ያሉት አቶ ሰለሞን፥ ስልጣኞች በቆይታቸው የወሰዱትን ግንዛቤ ወደስራ በመቀየር የተሻለ የመሪነት ሚናቸውን እንዲወጡ መልእክት አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ የሴቶች ማሕበራት ቅንጅት ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ሣባ ገ/መድህን በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ በመገኘት ለሰልጣኞች ልምዳቸውን አካፍለዋል። ሰልጣኞች በነበራቸው ቆይታ የተሻለ እውቀት እንዳገኙ ያላቸውን እምነት ገልፀው የሴቶችን የአመራርነት አቅም ከማጎልበት አኳያ መሠል ስልጠና የጎላ ፋይዳ ስላለው ወደፊትም ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል። በተጨማሪም ከዚህ በፊት ስልጠናውን የወሰዱ ሴቶች በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ክትትል እየተደረገ የሚደገፉበት ሁኔታ መመቻቸት እንዳለበት አመላክተዋል። በ2ኛው ዙር ከሁሉም ክልሎች እና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደር የተወጣጡ 35 ሴቶች የአቅም ግንባታ ስልጠናውን ወስደዋል።
